የሥርዓተ ምግብ ሽግግርን ለማሳለጥ የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ -ዶክተር ግርማ አመንቴ - ኢዜአ አማርኛ
የሥርዓተ ምግብ ሽግግርን ለማሳለጥ የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ -ዶክተር ግርማ አመንቴ
አዲስ አበባ፤ ጥር 22/2016 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የሥርዓተ ምግብ ሽግግርን ለማሳለጥ የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ ተናገሩ።
የሥርዓተ ምግብ ሽግግር ፍኖተ ካርታ አተገባበር ላይ ትኩረቱን ያደረገ አውደ ጥናት ዛሬ ተካሂዷል።
በግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢኒስቲትዩት አዘጋጅነት በተካሄደው አውደ ጥናት የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ ፣የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ፣ የኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ሽፈራው ተክለማርያምን ጨምሮ የተለያዩ የልማት አጋሮች ተሳትፈዋል።
ስርዓተ ምግብ በዋናነት ምርት ከማሳ ጀምሮ ተጠቃሚዎች ጋር እስኪደርስ ያለውን የማምረት፣ የማቀነባበር እንዲሁም ለገበያ የማቅረብ ሂደትን ያካተተ ነው፡፡
ሂደቱን ተከትሎ ደህንነቱ የተጠበቀና በንጥረ ነገር የበለጸጉ ምግቦችን ለተጠቃሚዎች ተደራሽ ማድረግ የሽግግር ሂደቱ አካል ናቸው።
ፍኖተ ካርታው ቴክኖሎጂን ፣የተቋማትንና የግብርና ኢንዱስትሪዎችን ቅንጅት ማጠናከር ፣የተፈጥሮ ሃብትን መንከባከብ እንዲሁም ለስርዓተ ምግብ መረጋገጥ የሚያስፈልጉ ሃብቶችን መመደብ ላይ ትኩረት ያደረገ ነው።
በኢትዮጵያም የስርዓተ ምግብ ሽግግር ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ ተግባራዊ በመደረግ ላይ ይገኛል፡፡
ፍኖተ ካርታውን የግብርና ሚኒስቴርና የጤና ሚኒስቴር በጋራ የሚመሩት ሲሆን 15 ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን ባቀፈ አብይ ኮሚቴ መዘጋጀቱ ተገልጿል።
የሚኒስትሮች አብይ ኮሚቴ ተልዕኮ ስርዓተ ምግብን ለማረጋገጥ የሚያስፈልጉ ኃብቶችን ማሰባሰብ ፣ በቅንጅት መስራትን እንዲሁም ለስርዓተ ምግብ መረጋገጥ የላቀ ሚና ያላቸው መርሃ ግብሮችና የመፍትሄ እርምጃዎች እንዲሳኩ ርብርብ ማድረግ ነው።
የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በዘላቂ ልማት ግብ ውስጥ የተካተተውን የስርዓተ ምግብ ተደራሽነት ለማሳካት አበረታች ስራዎችን እያከናወነች ትገኛለች።
ለዚህም ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ መልኩ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው ቴክኖሎጂዎችን ጨምሮ ዘመናዊ አሰራሮችን በመከተል ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ተናግረዋል።
የሚኒስትሮች አብይ ኮሚቴ በሥርዓተ ምግብ ዙሪያ በጋራ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው አሁንም ቅንጅት ላይ የበለጠ መስራት እንደሚገባ አመላካች ውጤቶች ታይተዋል ነው ያሉት።
በስርዓተ ምግብ ዙሪያ የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸው ለዚህም የባለድርሻ አካላትና የልማት አጋሮች ተሳትፎ ሊጠናከር እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በበኩላቸው ጤና ሚኒስቴር የምግብና የምግብ ዋስትና ስትራቴጂ በመንደፍ በርካታ ውጤታማ ተግባራት ማከናወኑን ጠቁመዋል።
የህጻናት፣እናቶችና ወጣቶች ሥርዓተ ምግብ ማሻሻል ትልቅ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን ጠቅሰው በሰቆጣ ቃል ኪዳን ትግበራ የተገኙ ተሞክሮዎችን ማስፋት ሌላው የትኩረት መስክ መሆኑን አብራርተዋል።
የህጻናት የመቀንጨር ችግርን ለመከላከል በተሰራው ሥራ ከ50 በመቶ በላይ የነበረውን የህጻናት የመቀንጨር ችግር ወደ 39 በመቶ ዝቅ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።
አሁንም በስርዓተ ምግብ ዙሪያ የሚስተዋሉ ችግሮች በርካታ በመሆናቸው ችግሩን ለመፍታት የባለድርሻ አካላት ቅንጅት መጠናከር ወሳኝ መሆኑን አስታውቀዋል ።
የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ማንደፍሮ ለማ በበኩላቸው የስርዓተ ምግብ ሽግግር ፍኖተ ካርታ ትግበራ ውጤትን ለመገምገም በተደረገ ጥናት ሦስት መሰረታዊ ጉዳዮች መለየታቸውን ተናግረዋል።
ከጥናት ግኝቱ መካከል የተለያዩ ተቋማት አንድ ዓይነት ሥራ ማከናወናቸው መለየቱን አስታውሰው ይህም የሃብት ብክነት እያመጣ መሆኑን አሳይቷል ብለዋል።
በአንዳንድ ተቋማት ላይ የታየው የሥርዐተ ምግብ አተገባበር ትኩረት ማነስ ከተለዩ ችግሮች መካከል እንደሚጠቀስ አብራርተዋል።
አውደ ጥናቱ በስርዓተ ምግብ ስራዎች ላይ የሚስተዋሉ ክፍቶችን በመለየትና የጋራ ውይይት በማድረግ ቀጣይ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ ያለመ መሆኑንም ገልጸዋል።
በዚሁ መሰረት የልማት አጋሮች ሚና እንዴት ይጠናከር? የትኛው ቦታ ላይ ኃብት ይመደብ ? የአተገባበር ክፍተት የታየባቸው ተቋማት ችግሮቹን እንዴት ያስተካከሉ? የሚሉ ጉዳዮች በስፋት እንደሚዳሰሱም አብራርተዋል።