የቤኔሉክስ ሀገራት ባለሃብቶች በኢትዮጵያ የተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች በስፋት እንዲሳተፉ እየተሰራ ነው - አምባሳደር ሒሩት ዘመነ - ኢዜአ አማርኛ
የቤኔሉክስ ሀገራት ባለሃብቶች በኢትዮጵያ የተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች በስፋት እንዲሳተፉ እየተሰራ ነው - አምባሳደር ሒሩት ዘመነ
አዲስ አበባ፤ ጥር 22/2016 (ኢዜአ)፦ቤኔሉክስ አገራት ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በሆርቲካልቸር፣ ፋርማሲውቲካል ኢንዱስትሪና ሌሎችም መስኮች በስፋት እንዲሳተፉ እየተሰራ መሆኑን አምባሳደር ሒሩት ዘመነ ገለጹ።
በቤልጂየም፣ ኔዘርላንድስ፣ ሉክሰምበርግ አገራትና በአውሮፓ ሕብረት የኢትዮጵያ አምባሳደር ሒሩት ዘመነ፤ የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ጥረት በተመለከተ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
በኢትዮጵያ በተለይም በቱሪዝም፣ ሆርቲካልቸርና ሌሎችም መስኮች ያሉ እምቅ ኃብቶች የውጭ ኢንቨስተሮች በስፋት እንዲሳተፉ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
በገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለሀገርና ገበታ ለትውልድ የተከናወኑ አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎችን ጨምሮ ሌሎችም አስደናቂ መስህቦች በስፋት እንዲታወቁ እየተደረገ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያን የቱሪዝም መስህቦችና የኢንቨስትመንት ዕድሎች ለአውሮፓ ሀገራት በማስተዋወቅ ረገድ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ዓመታዊው ''ብራስልስ ሆሊዴይ ፌር'' የቱሪዝም አውደ-ርዕይ በመሳተፍ በዚሁ አጋጣሚ ኢትዮጵያን የማስተዋወቅ ሥራ ዋነኛው ትኩረት መሆኑን ገልፀዋል።
በዚህም የቤኔሉክስ ሀገራት ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በሆርቲካልቸር፣ ፋርማሲውቲካል ኢንዱስትሪና ሌሎችም መስኮች በስፋት እንዲሳተፉ የማስተዋወቅ ሥራ ይሰራል ብለዋል።
በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች የሚሰማሩ ባለሃብቶች መልካም ዕድሎችን እንዲጠቀሙ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም አምባሳደሯ ገልፀዋል።
ለ65ኛ ጊዜ ዘንድሮ የሚካሄደው ''ብራስልስ ሆሊዴይ ፌር'' ዓለም አቀፍ የቱሪዝም አውደ-ርዕይ ከ100 ሺህ በላይ ጎብኚዎች እንደሚገኙ ይጠበቃል።
ከዚህ ቀደም በተካሄዱ የ“ብራስልስ ሆሊደይ ፌር” አውደ-ርዕይ ኢትዮጵያ የቱሪዝም ኃብቶችና የኢንቨስትመንት አማራጮችን አስተዋውቃለች ተብሏል።