ቀጥታ፡

“ፀሐይ” ("ኢትዮጵያ-1”) ማናት?

አየለ ያረጋል

'ፀሐይ' ሰማየ-ሰረገላ ናት። የ'ጢያራ'ዋ ሌላው ስም 'ኢትዮጵያ 1' ይሰኛል። በርግጥ ኢትዮጵያ ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ በፊት አይነተ ብዙ አውሮፕላኖችን ገዝታ ነበር። በኢትዮጵያ አቪዬሽን ታሪክ ነሐሴ 12 ቀን 1921 ዓ.ም በኢትዮጵያ ሰማይ የበረረች የመጀመሪያዋ አውሮፕላን የፈረንሳይ ስሪት የሆነችው እና 'ንሥረ ተፈሪ' በሚል የተሰየመችው ፖቴዝ አውሮፕላን ናት። የኋላዋ 'ንሥረ ተፈሪ' ገፈርሳ አካባቢ ስታርፍ የአዲስ አበባ ህዝቡ በወቅቱ አጠራር 'የሠማይ ባቡር' ለማየት የነበረው ጉጉት አጃኢብ እንደነበር መርስዔ ሀዘን ወልደቂርቆስ ዘግበዋል።

ቀጥሎም ስሪታቸው በተለያዩ ሀገራት የሆኑ እንደ ርግበ ተፈሪ (በኋላ ደሴ)፣ ሐረር፣ አባ ቃኘው፣ አባ ዳኘው፣ አዲስ አበባ፣ ንስረ-አስፋወሰን እና ሌላ ስያሜዎች የነበሯቸው አውሮፕላኖች እንደነበሩ ዕሙን ነው። በጥቅሉ ከወረራው በፊት ኢትዮጵያ 15 አውሮፕላኖች ነበሯት።

ነገር ግን ከ88 ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ አውሮፕላን ስለመሰራቱ ያውቁ ኖሯል? አዎ 'ፀሐይ' ጃንሜዳ ውስጥ የተሰራች አውሮፕላን ናት። ሁለገቡ ጃንሜዳ መቼስ በታሪክ ገፅ ጉልህ ስፍራ ይዟል። 

የአውሮፕላንን ጥቅምና ጣዕም በቅጡ የተረዱት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ከተለያዩ ሀገራት ባለሙያዎችን በማስመጣት ኢትዮጵያዊያንን አብራሪነትና የጥገና ሙያ እንዲያሰለጥኑ ማድረግ የጀመሩት አውሮፕላን ኢትዮጵያ ውስጥ በገባ ማግስት ነበር። 

ጀርመናዊው መሀንዲስ እና አብራሪ ሉድዊግ ቬበር (Ludwig Weber) ኢትዮጵያ ውስጥ አውሮፕላን በመገጣጠም እና በመጠገን ስራ የተቀጠረ ባለሙያ ነበር። በወቅቱ በቅኝ ገዥዎች ሴራ ተጨማሪ አውሮፕላን ለመግዛት የነበረውን ፈተና ለማስወገድና የኢትዮጵያን አቪዬሽን ዘርፍ ለመገንባት ኢትዮጵያ ውስጥ አውሮፕላን የመስራት ውጥን በቬበርና ኢትዮጵያዊ ጓዶቹ ጥረት ተጀመረ። 

ሞተርና ጥቂት ዕቃዎች ከውጭ በማስመጣት በሀገር ውስጥ ሶስት አውሮፕላን ለማምረት ሥራው ተጀመረ። ሉድዊግ ቬበር በስሩ ቢለ፣ በረንት እና ሀስ የተባሉ ጀርመናውያን እንዲሁም ዓምደወርቅ አሊ፣ ሰንበቶ ገኖ፣ ኪዳኔ ገብረፃዲቅ፣ ተገኝና መሰል ኢትዮጵያዊያን መካኒኮችን በመያዝ አፄ ኃይለሥላሴ ገንዘብ ድጋፍ የአውሮፕላን ስራውን አፋጠነ። በእንጨት የተዋቀረች፣ በሸራ መሳይ ጨርቅ የተለበደች አውሮፕላን ጃንሜዳ ተሰራች።  ንጉሠ ነገሥቱም በልጃቸው ልዕልት ፀሐይ ስም "ፀሐይ" ብለው ሰየሟት።

ካፒቴን ዘላለም አንዳርጌ "ፀሐይ፦ የኢትዮጵያ አቪዬሽን አጀማመር" በተሰኘ መፅሐፋቸው እንደገለፁት ፀሐይ ከፊትና ከኋላ ሁለት መቀመጫ ኖሯት የመቀመጫና ጋቢናዋ ውስጣዊ ግድግዳዎች በጥጥ እና ባማረ ቆዳ የተሸፈኑ ነበሩ። አጠቃላይ ውጫዊ ገፅታዋን በተመለከተ በመፅሐፋቸው ገፅ-187 ላይ እንዲህ ገልፀውታል።

"አውሮፕላኗ ሙሉ በሙሉ ብርማ ግራጫ የተቀባች ሰትሆን በሁለቱም ክንፎቿ የላይኛው አካልና እንዲሁም ጭራዋ ላይ በግራና በቀኝ የኢትዮጵያ ባንዲራ ዓርማ የሆነውን አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለም ከሩቅ እንዲታይ ሆኖ ተቀብታለች። በክንፎቿና በጭራዋ አማካይ ቦታ ላይ በሚገኘው የአውሮፕላኗ አካል ላይ "ፀሐይ" የሚለው ስያሜዋ በአማርኛ ፊደሎች በጉልህ በግራና በቀኝ ተፅፎ ይገኛል። በተጨማሪም በአማርኛ "ኢትዮጵያ 1" እንዲሁም በእንግሊዘኛ (የላቲን) ፊደሎች "Ethiopia 1" በሚል የጭራዋ ቋሚ አካል ላይ በግራና በቀኝ በኩል በቀይ ቀለም ተፅፎባታል" ብለዋል።

'ፀሐይ' ታኅሣሥ 1928 ዓ.ም ሥራዋ ተጠናቆ በቬበር አማካኝነት የመጀመሪያ የበረራ ሙከራ አድርጋለች። ቬበር ከጃንሜዳ ተነስቶ 50 ኪሎ ሜትር ከከተማ ወጣ ብሎ ተመለሰ። ፀሐይን በሰዓት ከ230 እስከ 240 ኪሎሜትር በማብረር ፈተሻት። በወቅቱም ፀሐይ ከጠበቃት በላይ ከጥሩ አውሮፕላን ተርታ የምትመደብ እንደሆነች ፈልሳሚዋና አብራሪዋ ቬበር በግርምታ ገልጾ ነበር። 

የስራው ተካፋይ የነበሩት ዓምደወርቅ አሊ ክስተቱን በ1950ዎቹ ለታተመ መፅሔት በሰጡት ቃለ መጠይቅ "...የሁላችንም ደስታ ታላቅ ሆነ። የጀመርነው ጉዞ ተፈፀመ። ሀገራችን ውስጥ አውሮፕላን ሰርተን ማብረር ስንጀምር የማይጨው ነጋሪት ተጎሰመ" ሲሉ የፀሐይን አሳዛኝ ዕጣ ፈንታ ገልፀዋል። ከፀሐይ ቀጥሎ የተጀመሩ አውሮፕላኖች ስራም ተስተጓጎለ። 

ፋሺስት ኢጣሊያ አዲስ አበባን ከተቆጣጠረች በኋላ 'ፀሐይ' ወይም "ኢትዮጵያ 1" ጃንሜዳ ውስጥ በቁጥጥር ስር ዋለች። ቀጥሎም እንደ አክሱም ሐውልት በመርከብ ተጭና አውሮፓ-ኢጣልያ ገባች። የፀሐይ ነገር 'መፅሐፉም፣ ቄሱም ዝም' ሆነ ።

በዚህም ፀሐይ በታሪክ ሊቃውንት እና ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስትን መሰል የኢትዮጵያ ቅርስ ተቆርቋሪ ግለሰቦች በስተቀር እምብዛም ስሟም፣ ማንነቷም አይታወቅም። ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ጨለማ ውስጥ የተደበቀችው ፀሐይ፣ ፀሐይ ይወጣላት ዘንድ በዘመናቸው ድምፃቸውን አሰምተዋል።

ቅኝ ገዥዎች ከአፍሪካ የዘረፏቸውን ቅርሶች እንዲመልሱ በ1939 ዓ.ም የተፈረመው የጀኔቫ ስምምነት ቢደግፋቸውም ቅኝ ገዥዎች ግን በርካታ ቅርሶችን መመለስ አልቻሉም። ኢትዮጵያም በተለያዩ ዘመናት ተዘርፈው ተወስደው በአውሮፓ ሀገራት ሙዚየሞች የሚገኙ ቅርሶቿ ዕልቆ መሳፍርት እንደሌላቸው ይነገራል። ከነዚህም ቅርሶች መካከል አንዷ 'ፀሐይ' የተሰኘችው የኢትዮጵያዊያን ጠቢባን አሻራ ያረፈባት አውሮፕላን ትገኝበታለች። 

ፀሐይ ወደ እናት ሀገሯ ባትመለስም ግን ኢጣሊያ ውስጥ ከተደበቀችበት ወጥታ ሙዚየም ውስጥ ለጉብኝት ውላ ታውቃለች። 

ካፒቴን ዘላለም አንዳርጌ ወደ ሮም በማቅናት 'ፀሐይን' የማየት ዕድል ገጥሟቸዋል። ፀሐይ የምትገኘው ከሮም ከተማ በስተሰሜን ምዕራብ 32 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው 'ቪኛ ዲቫሌ' በተሰኘው የጣሊያን አየር ኃይል ሙዚዬም እንደሆነ ካፒቴኑ በመፅሐፋቸው ገልፀዋል። ከብዙ ውጣ ውረድና ጥረት በኋላ ሙዚየሙ ውስጥ ተገኝተው ፀሐይን ለማየት በቻሉበት ወቅት የተሰማቸውን ስሜት ሲገልፁ፤

"ዙሪያውን በዓይኔ ስቃኝ ድንገት ፀሐይን አየኋት። ደማቅ የሆነ ቀይ ቀለሟ ከሩቅ ይስባል። ከሌላ መጋዘን እንደመጣች ያስታውቃል። በሚገባ ፀድታ በጣም ታምር ነበር። .... በሕይወቴ እጅጉን የጓጓሁለት ነገር ስለነበረች በዝግታ እያንዳንዱን ነገር ጠጋ በማለት ፈዝዤ ማየት ጀመርኩ። በመሀል ቬበር የኋላው ወንበር ላይ ቁጭ ብሎ ታየኝ። የሞተሩን ድምፅ፣ ጃንሜዳ፣ የሀገሬ ሰው ከነአለባበሱ ተመላለሱብኝ" ይላሉ።

ፀሐይ ከኢትዮጵያ ወደ ጣሊያን ስትወሰድ ብርማ ግራጫ ቀለም ነበራት። በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ወቅት አሁን የምትገኝበት ሙዚየም ከመገንባቱ በፊት በተለያዩ አየር ኃይል ስፍራዎች ተዘዋውራለች። በ1950ዎቹ ስትታደስ ደማቅ ቀይ ቀለም መልክ ይዛለች። በ1969 አሁን የምትገኝበት ሙዚየም ገባች። እስከ የካቲት 2010 ዓ.ም ድረስ ደግሞ በሙዚየሙ ቦታ ጥበት ሳቢያ ክንፎቿ ተነቃቅለው መጋዝን ውስጥ ነበሩ። ከዛ ወዲህ ግን ዕድሳት ተደርጎላታል።

ፀሐይ በዓለም ላይ በአይነቷ ብቸኛ ናት። ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በፊት በኢትዮጵያ የተሰራች ብቸኛ አውሮፕላን ስትሆን የመስሪያ ቦታ፣ መሳሪያ እና ግብዓት ባልተሟላበት በሀገሬው አናፂዎች ዕጅ የተሰራች መሆኗም ልዩ ያደርጋታል። 

ፀሐይ ብዙ የአካል ክፍሏ በሀገርኛ ቁሳቁስ የተሰራች ሲሆን ለምሳሌ መሪዋ የተሰራው ከቀንድ ነው። ካፒቴን ዘላለም ፀሐይ በጭራዋና በክንፎቿ ላይ የኢትዮጵያን ሠንደቅዓላማ አድምቃ፣ 'ኢትዮጵያ 1' ተብሎ ተፅፎባት ብትመለስ ምንኛ አስደሳች ነበር በማለት በቁጭት ፅፈዋል። ፀሐይን ማስመለስ ከባድ ትግል እንደሚጠይቅም ጠቁመው ነበር።

ይህችን ታሪካዊ አውሮፕላን ወደ ኢትዮጵያ ለማስመለስ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ከጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጂኦርጂነያ ሜሎኔ ጋር ለዓመት የዘለቀ ሰፊ ንግግር ሲያደርጉ ቆይተዋል። 

እነሆ ቀኑ ደርሶ የጣልያን መንግሥት "ፀሐይ"ን ለኢትዮጵያ መንግሥት ያስረከበበት የታሪካዊ ሁነት ትላንት ተከናውኗል። ፀሐይ ወደ እናት ሀገሯ ልትመለስ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አብስረዋል።

ይሄውም ከ68 ዓመታት በኋላ (በ1997 ዓ.ም) ከተመለሰው የአክሱም ሐውልት ቀጥሎ ትልቋ ቅርስ ፀሐይ ሮም ውስጥ ከታሰረች ከ87 ዓመታት በኋላ የተመለሰች ድንቅ ቅርስ ያደርጋታል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የ"ፀሐይ" ወደ ኢትዮጵያ መመለስ ያለውን ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ገልጸዋል። ታሪካዊ ሁነቱንም 'የታሪክ ስብራቶችን የመጠገን ጥረቶቻችን ማሳያ' ብለውታል። ለአውሮፕላኗ መመለስ የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጂኦርጂነያ ሜሎኔን አመስግነዋል።

በተለያዩ የዓለም ሀገራት የሚገኙ የኢትዮጵያን ቅርሶችና ሃብቶች በማስመለስ የኢትዮጵያን የታሪክ ስብራቶች በመጠገን ዕድገትና ብልጽግናዋን ለማረጋገጥ የሚደረገው ጥረትም ተጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል።

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም