ባለፉት ስድስት ወራት የሳይበር ጥቃቶችን በመከላከል ከ10 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ ማዳን ተችሏል - ኢንሳ - ኢዜአ አማርኛ
ባለፉት ስድስት ወራት የሳይበር ጥቃቶችን በመከላከል ከ10 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ ማዳን ተችሏል - ኢንሳ

አዲስ አበባ፤ ጥር 22/2016 (ኢዜአ)፦ ባለፉት ስድስት ወራት ወደ ሀገር የተሞከሩ የሳይበር ጥቃቶችን በመከላከል ከ10 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ ማዳን መቻሉን የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር /ኢንሳ/ ገለጸ።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር /ኢንሳ/ የ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸሙን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
መግለጫውን የሰጡት ዋና ዳይሬክተሩ ሰለሞን ሶካ እንዳስታወቁት፤ ባለፉት ስድስት ወራት የሳይበር ጥቃትን ከመከላከል አንጻር የተሻሉ ሥራዎች ተከናውነዋል።
በዚህም በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት 4 ሺህ 623 የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች መሰንዘራቸውን ገልጸው፤ ከተሰነዘሩት ውስጥ 98 ነጥብ 56 በመቶ የሚሆኑትን ማክሸፍ መቻሉን ገልፀዋል።
የተሞከሩት ጥቃቶች መሠረተ-ልማትን ማቋረጥ፣ አገልግሎትና ገቢን የማስተጓጎል ሙከራ፣ የዳታ ሥርቆትና መጥፋት እንዲሁም የክፍያ መንገድን በመጠቀም ማጭበርበርን ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በሳይበር ጥቃቱ ዒላማ ከተደረጉ ተቋማት መካከልም ባንኮችና የፋይናንስ ተቋማት፣ የሚዲያና ቁልፍ የመንግሥት ተቋማት፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችና የክልል ቢሮዎች ይጠቀሳሉ ብለዋል።
ከሳይበር ጥቃት ዓይነቶቹ መካከል የድረ-ገጽ ጥቃት፣ ማልዌር፣ የመሠረተ-ልማት ቅኝት እንዲሁም የመሠረተ-ልማት ማቋረጥ እንደሚገኙበት ጠቁመዋል።
በሌላ መልኩ ባለፉት ስድስት ወራት በ149 ተቋማት ላይ የሳይበር ደኅንነት ተጋላጭነት የዳሰሳ ጥናት መከናወኑን ዋና ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል።
ይህም በ110 የግል እና በ39 የመንግሥት መሥሪያ ቤት ተቋማት ላይ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡
በተጨማሪም አስተዳደሩ የመረጃ እና መገናኛ ቴክኖሎጂዎች ቁጥጥር በማድረግ ወደ ሃገር ውስጥ ለማስገባት ፈቃድ ከተጠየቀባቸው 2 ሺህ 999 የተለያዩ ዓይነት ቴክኖሎጂዎች መካከል 335 የሚሆኑት የደኅንነት ስጋት ያለባቸው በመሆኑ እንዳይገቡ መከልከላቸውን ጠቁመዋል።
በአጠቃላይ ባለፉት ስድስት ወራት ከተሞከሩ የሳይበር ጥቃቶችን በመከላከል ከ10 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ ማዳን መቻሉን ዋና ዳይሬክተሩ ገልፀዋል፡፡