ቀጥታ፡

ኢዜአ ''የመደመር ጉዞ'' በሚል የመደመር እሳቤን ለማስረጽ እያካሄዳቸው ያሉ መድረኮች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል - የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ፤ ጥር 22/2016 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት  ''የመደመር ጉዞ'' በሚል የመደመር እሳቤን ለማስረጽ እያካሄዳቸው ያሉ መድረኮች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ   የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ድኤታ ከበደ ዴሲሳ ገለጹ።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ድኤታ ከበደ ዴሲሳ ፣ኢዜአ ባለፉት 82 ዓመታት የኢትዮጵያ የመረጃ ቋት በመሆን ሲያገለግል ቆይቶ በአዲስ ምዕራፍ ወደ ስራ መግባቱ የሚደነቅ ነው ብለዋል።

ኢዜአ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) የመደመር መጽሃፍን መነሻ በማድረግ የተለያዩ የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት ለብሄራዊ መግባባትና ሀገራዊ አንድነት እውን መሆን ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ አንስተዋል።

ይህ ጥረት በማህበረሰቡ ዘንድ የመደመር እሳቤን በማስረጽ በሀገር በቀል እውቀት ኢትዮጵያ የራሷን ችግሮች የምትፈታበትንና ወደፊት የምትመራበትን አቅጣጫ ለማመላከት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የተጀመሩት ''የመደመር ጉዞ '' መድረኮች በተሻለ አቀራረብ ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ሲሉ ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ በበኩላቸው፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በመደመር መጽሃፋቸው ሚዲያዎች ውስጣዊ ብቻ ሳይሆን ውጭያዊ እይታ ሊኖራቸው እንደሚገባ ማንሳታቸውን ተናግረዋል፡፡

በዚህ ረገድ ኢዜአ የመደመር እሳቤ ለኢትዮጵያዊያን አብሮነትና ሁለንተናዊ እድገት ያለውን ፋይዳ በመረዳት፣ እንደ አንድ ብሄራዊ የዜና አገልግሎት እሳቤውን ለማስረጽ ይሰራል ብለዋል።

ኢዜአ ''በመደመር ጉዞ'' በተለያዩ የሀገሪቷ የክልል ከተሞች በመዘዋወር 7 መድረኮችን ያካሄደ ሲሆን መድረኮቹ ሀገራዊ አንድነትንና ብሄራዊ መግባባትን በማስረጽ ረገድ ውጤታማ እንደነበሩ ገልጸዋል።

በቀጣይ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከሀገር ውጭ መሰል መድረኮችን ለማዘጋጀት ዕቅድ ይዞ እየሰራ እንደሚገኝ ዋና ስራ አስፈጻሚው አስታውቀዋል።

በዚህም ተከታታይ መድረኮችን በማዘጋጀት ኢዜአ በሀገረ መንግስት ግንባታ ውስጥ የሚጠበቅበትን ሚና በትጋት መፈጸሙን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል። 

ከተመሠረተ 82 ዓመታት የሞላው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ያስገነባውን ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት ትናንት ማስመረቁ ይታወሳል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም