ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የይዘት ስራዎቹን ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ አለምአቀፍ የሚዲያ ትስስሮችን እየፈጠረ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥር 22/2016 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የይዘት ስራዎቹን ተደራሽነት  ይበልጥ ለማሳደግ  ከተለያያ ዓለምአቀፍ የሚዲያ ተቋማት ጋር ትስስርና አጋርነት ፈጥሮ እየሰራ መሆኑን የተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ ገለጹ። 

ከተመሰረተ 82 ዓመታትን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ያስገነባውን ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስ አስመርቋል።

የሚዲያ ኮምፕሌክሱ ዘመኑ የደረሰበትን የሚዲያ ቴክኖሎጂ ያሟላ ሲሆን ሦስት የቴሌቪዥንና አራት የሬዲዮ ዘመናዊ ስቱዲዮዎች አሉት።

በተጨማሪም ለቢሮ አገልግሎት የሚሆኑ ክፍሎች፣ የመሰብሰቢያ አዳራሾች ቤተመፅሐፍት፣ የመዝናኛ ማዕከልና ዘመናዊ ጂምናዝየም ያካተተ ነው።

የተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ ኢዜአ ብሔራዊ መግባባትን የሚያጠናክሩ፣ ለአገር ገጽታ ግንባታ አስተዋጽኦ የሚያደርጉና የመንግስትን የትኩረት አቅጣጫዎች ታሳቢ ያደረጉ ስራዎች እየሰራ ነው ብለዋል።

ተቋሙ በህዝብና በመንግስት የተጣለበትን ሃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት በየጊዜው ሲያጋጥሙት የነበሩ ፈተናዎችን እያለፈና ራሱን እያሻሸለ መምጣቱንም ተናግረዋል።

ኢዜአ በተለይም የአገርን ገጽታ ለመገንባት የሚሰራቸውን ስራዎች ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ ከአለምአቀፍ የሚዲያ ተቋማት ጋር ትስስር እየፈጠረ መሆኑንም አንስተዋል።

ለተቋሙ ለውጥ ደግሞ መንግስት ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) የቻይናው (XINHUA) ፣ ከጣሊያን ዜና አገልግሎት ( ANSA)፣  ከሩሲያው (SPUTNIK) ሚዲያ ግሩፕ ጋር በትብብር ለመስራት የተፈራረማቸውን ስምምነቶች ለአብነት ማንሳት ይቻላል።

እንደ አቶ ሰይፈ ገለጻ፣ኢዜአ በአንኳር አገራዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን በማጠናከር ሕዝቦችን ይበልጥ በሚያቀራርቡና የአገሪቱንም እድገት በሚያፋጥኑ ጉዳዮች ላይ  ለመስራት የሚያስችለውን የቴክኖሎጂና የሰው ሃይል ማጠናከር ላይ ትኩረት አድርጓል።

በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተደራሽና ተመራጭ የዜና ወኪል ለመሆን ከቋንቋ ስብጥር ጀምሮ  ጠንካራ ይዘት ይዞ መውጣት ወሳኝ መሆኑንም አንስተዋል።

ተቋሙ በቀጣይም ከአገርና ህዝብ የተሰጠውን ሃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት የሰው ሃይሉን በማጠናከር  ተልዕኮውን ለመወጣት በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

ከተመሠረተ 82 ዓመታትን የተሻገረው አንጋፋው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ብሔራዊ መግባባት የመፍጠርና የሀገር ገፅታ ግንባታ ተልዕኮውን ለማሳካት ዜና እና ዜና ነክ መረጃዎችን ተደራሽ በማድረግ ላይ ይገኛል።

ለዚህም በመላው ሀገሪቱ 38 ቅርንጫፎችን በመክፈት በቅርቡ የጀመራቸውን ሶማሊኛ እና አፋርኛ ጨምሮ በአማርኛ፣ በአፋን ኦሮሞና በትግርኛ ቋንቋዎች ዜናና ዜና ነክ መረጃዎችን እያቀረበ ይገኛል።

በእንግሊዝኛ፣ በአረብኛ እና በፈረንሳይኛ ቋንቋዎችም የኢትዮጵያን አሁናዊ ገፅታና እውነታ ለዓለምአቀፉ ማህበረሰብ ተደራሽ እያደረገ ነው።

ኢዜአ በ2022 በአፍሪካ ተምሳሌት፣ አስተማማኝና ተጽዕኖ ፈጣሪ የዜና ምንጭ የመሆን ራዕዩን ለማሳካት በላቀ ብቃት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም