"ፀሐይ" አውሮፕላን ወደ ኢትዮጵያ መምጣቷ የታሪክ ስብራቶችን የመጠገን ጥረቶቻቸን ማሳያ ነው-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ - ኢዜአ አማርኛ
"ፀሐይ" አውሮፕላን ወደ ኢትዮጵያ መምጣቷ የታሪክ ስብራቶችን የመጠገን ጥረቶቻቸን ማሳያ ነው-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
አዲስ አበባ፤ ጥር 22/2016(ኢዜአ)፦ "ፀሐይ" አውሮፕላን ወደ ኢትዮጵያ መምጣቷ የታሪክ ስብራቶችን የመጠገን ጥረቶቻቸን ማሳያ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር (ዶ/ር ) ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ።
ከሁለተኛው የአለም ጦርነት በፊት በጀርመናዊው ኢንጂነር ሄር ሉድዊግ ዌበር እና በኢትዮጵያዊያን ባለሞያዎች በ1928 ዓ.ም በኢትዮጵያ የተገጣጠመችው "ፀሐይ" አውሮፕላን በ1929 ዓ.ም ወደ ጣሊያን መወሰዷ ይታወሳል።
በመሆኑም ይህችን ታሪካዊ አውሮፕላን ወደ ኢትዮጵያ ለማስመለስ ጠቅላይ ሚኒስትር (ዶ/ር) ዐቢይ አህመድ ከጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጂኦርጂነያ ሜሎኔ ጋር ሰፊ ንግግር ሲያደርጉ ቆይተዋል።
በዚህም መሰረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በይፋ ተረክበው "ፀሐይ" ወደ ሀገሯ እንድትመለስ ማድረግ ችለዋል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር (ዶ/ር) ዐቢይ አሕመድ፤ "ፀሐይ" ከ88 ዓመታት በፊት ወደ ጣሊያን ተወስዳ ቆይታ ወደ ኢትዮጵያ መመለሷ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ አለው ብለዋል።
የ"ፀሐይ" መመለስ በሁሉም መልኩ የኢትዮጵያን የታሪክ ስብራቶች የመጠገን ሂደት እየተሳካ መሆኑን የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።
በ1928 ዓ.ም የተገጣጠመችው "ፀሐይ" አውሮፕላን ኢትዮጵያ በዘመኑ የነበራትን የቴክኖሎጅ ልቀትና ቅርበት የሚያሳይ መሆኑን ጠቅሰው እንዲህ አይነት ጉልህ ታሪኮችን በማስቀጠል የታሪክ ስብራቶችን በመጠገን ልእልናዋን ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።
አውርፕላኑን በማስመለስ ረገድ የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ለነበራቸው ቀና ትብብርና የላቀ አስተዋጽኦም ምስጋና አቅርበዋል።
በተለያዩ የዓለም አገራት የሚገኙ የኢትዮጵያን ቅርሶችና ሃብቶች በማስመለስ የኢትዮጵያን የታሪክ ስብራቶች በመጠገን እድገትና ብልጽግናዋን ለማረጋገጥ የሚደረገው ጥረትም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በጀርመናዊው ኢንጅነር ሄር ሉድዊግ ዌበር እና የኢትዮጵያ ባለሞያዎች ትብብር የተሰራችው "ፀሐይ" አውሮፕላን በጠቅላይ ሚኒስትር (ዶ/ር) ዐቢይ አህመድ የዲፕሎማሲ ጥረት ወደ ኢትዮጵያ መመለስ ችላለች።