ኢዜአ አንጋፋነቱን የሚመጥን የይዘት ስራና የሰው ኃይል ይፈልጋል- የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት - ኢዜአ አማርኛ
ኢዜአ አንጋፋነቱን የሚመጥን የይዘት ስራና የሰው ኃይል ይፈልጋል- የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት
አዲስ አበባ፤ ጥር 22/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አንጋፋነቱን የሚመጥን የይዘት ስራና የሰው ኃይል ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት እንዳለበት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት አመራሮች ገለጹ።
ከተመሰረተ 82 ዓመታትን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ያስገነባውን ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስ ትላንት አስመርቋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት የስራ አስፈፃሚ ሰብሳቢ አቶ አማረ አረጋዊ ኢዜአን ጨምሮ የተለያዩ ሚዲያዎችን በመምራትና በማቋቋም በሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ታሪክ ትልቅ አሻራ አሳርፈዋል።
ኢዜአ የሚዲያ ኮምፕሌክሱን ባስመረቀበት ዝግጅት የታደሙት አቶ አማረ አረጋዊ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አሁን ወደ ሚገኝበት ደረጃ እንዲደርስ ምኞት እንደነበራቸው ያነሳሉ።
አሁን ላይ ያስገነባው የሚዲያ ኮምፕሌክስ የያዛቸው ስቱዲዮች እና ቴክኖሎጂዎች እንዳስደነቃቸው ገልጸዋል።
ነገር ግን ከሕንጻ ግንባታ ባሻገር ህዝቡን መያዝና ተማራጭ መሆን የሚቻለው በይዘት ስራ በመሆኑ ኢዜአ በሰው ኃይል ግንባታ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት ጠቁመዋል።
የምክር ቤቱ ስራ አስፈጻሚ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ታምራት ሃይሉ ኢዜአ በርካታ የአፍሪካ አገራት በቀኝ ግዛት በነበሩት ወቅት ቀደምት ሚዲያ እንደሆነ ይገልጻሉ።
በአሁናዊ ቁመናውም አንጋፋነቱን የሚመጠን ይዘት እንደሚያሻው ገልፀው፣ ትክክለኛ፣ ታማኝና ወቅታዊ መረጃዎችን ተደራሽ ማድረግ ይጠበቅበታል ብለዋል።
አዲስ ያስመረቀው የሚዲያ ኮምፕሌክስም ከዚህ በኋላ በመሳሪያና በሕንፃ ዕጦት ምክንያት ስራዎች እንዳይስተጓጎሉ እንደሚያግዘው አንስተዋል።
ኢዜአ በይዘት ልቆ ከወጣ ተደራሽነቱን ማስፋት እንዲሁም ከኢትዮጵያ አልፎ በአፍሪካ ተወዳዳሪ እንደሚሆን አንስተዋል።
በተደራሽነት በኩል መላ ሀገሪቱን ያማከለ መረጃዎች ለህዝብ ተደራሽ ለማድረግ ይበልጥ መስራት እንዳለበት ገልጸዋል።
የኢዜአ የሚዲያ ኮምፕሌክስ ዘመኑ የደረሰበትን የሚዲያ ቴክኖሎጂ ያሟላ እና ሶስት የቴሌቪዥን እና አራት የሬዲዮ ስቱዲዮዎችን ያካተተ ነው።
በተጨማሪም ለቢሮ አገልግሎት የሚሆኑ በርካታ ክፍሎች፣ የመሰብሰቢያ አዳራሾች ቤተ-መፅሕፍት፣ የመዝናኛ ማዕከልና ዘመናዊ ጂምናዝየምም አሉት።