20ኛው የአፍሪካ ባለ ልዩ ጣዕም የቡናዎች ጉባኤና ኤግዚቢሽን በአዲስ አበባ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
20ኛው የአፍሪካ ባለ ልዩ ጣዕም የቡናዎች ጉባኤና ኤግዚቢሽን በአዲስ አበባ ይካሄዳል
አዲስ አበባ ፤ጥር 22/2016 (ኢዜአ)፦20ኛው የአፍሪካ የባለ ልዩ ጣዕም ቡናዎች ሳምንትና ኤግዚቢሽን ከጥር 28 ጀምሮ በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ።
የቡና ሳምንትና ኤግዚቢሽን ከጥር 28 ጀምሮ ለተከታታይ አምስት ቀናት በሚሊኒየም አዳራሽ ይካሄዳል።
የኢትዮጵያ ቡናናሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ እንዳሉት በመርሃ ግብሩ ላይ ከ25 አገራት የተውጣጡ 800 የሚሆኑ ቡና አምራችና ገዥ ድርጅቶች ይሳተፋሉ።
መርሃ ግብሩ ኢትዮጵያ የቡና ሃብቷን የምታስተዋውቅበት፣ ቡና አምራች አርሶ አደሮች ምርታቸውን በማስተዋወቅ ለውጪ ገበያ እንዲያቀርቡ የገበያ ትስስር የሚፈጠሩበት እንደሆነም ተመላክቷል።
ከተለያዩ አገራት የሚመጡ እንግዶችም በሲዳማና በኦሮሚያ ክልሎች የሚገኙ ቡና አምራች አካባቢዎችን እንደሚጎበኙ ዋና ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።
ጉባኤው "Speciality Coffee at Origin" በሚል መሪ ሃሳብ እንደሚካሄድና፤ በጉባኤውና ኤግዚቢሽኑም ዓለም አቀፍ የቡና ገዥዎች፣ ምሁራንና ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች እንደሚታደሙ ታውቋል፡፡