የተደራጀና ዘመናዊ የሚዲያ ተቋም በመገንባት ሀሰተኛ መረጃን በማምከን ፈጣን የተሟላና ትክክለኛ መረጃ ለህዝብ ተደራሽ ማድረግ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የተደራጀና ዘመናዊ የሚዲያ ተቋም በመገንባት ሀሰተኛ መረጃን በማምከን ፈጣን የተሟላና ትክክለኛ መረጃ ለህዝብ ተደራሽ ማድረግ ይገባል
አዲስ አበባ ፤ጥር 22/2016 (ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ የተደራጀና ዘመናዊ የሚዲያ ተቋም በመገንባት ሀሰተኛ መረጃን በማምከን ፈጣን የተሟላና ትክክለኛ መረጃ ለህዝብ ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ሰለሞን ሶካ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ያስገነባውን ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና የዘርፉ አንጋፋ ባለሙያዎች በተገኙበት አስመርቋል።
በምርቃት ስነ ስርአቱ ላይ የተገኙት የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ሰለሞን ሶካ፤ አሁን ላይ በተለይም በማህበራዊ ሚዲያዎች የሀሰተኛ መረጃ ስርጭት እየተስፋፋ መጥቷል ብለዋል።
በኢትዮጵያ የተደራጀና ዘመናዊ የሚዲያ ተቋም በመገንባት ሀሰተኛ መረጃን በማምከን ፈጣን የተሟላና ትክክለኛ መረጃ ለህዝብ ተደራሽ ማድረግ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
በዚህ ረገድ ኢዜአ በዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስ፣ በአዲስ ቴክኖሎጂ፣ በአዲስ ምእራፍ ወደ ስራ መግባቱ ትልቅ የለውጥ እርምጃ መሆኑን ገልጸዋል።
በአፍሪካ ተምሳሌት፣ አስተማማኝና ተጽዕኖ ፈጣሪ የዜና ምንጭ ለመሆን የሚያደርገውን ጥረት ለማሳካትም ትክክለኛ አቅጣጫ ላይ መሆኑን የሚያሳይ ነው ብለዋል።
በመሰረተ ልማት ግንባታ፣ በቴክኖሎጂና በሰው ሃይል ራሱን ይበልጥ በማጠናከርና በማደራጀት ወቅታዊ፣ ተዓማኒና ትክክለኛ መረጃ ተደራሽ የማድረግ ጥረቱን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።
የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ወርቁ ጋቸና፤ ኢዜአ በአዲስ ምእራፍ የከፍታ ጎዞ መጀመሩን አድንቀዋል።
ለጀመረው ጥረት ስኬት በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ መታገዘ እንዳለበት ጠቁመው ለዚህም ተቋማቸው አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍና እገዛ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
ኢዜአ በ82 ዓመታት የአገልግሎት ዘመኑ በአገሪቱ በተመዘገቡ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ስኬቶች ላይ የራሱን አሻራ ያሳረፈና እያሳረፈ ያለ ተቋም ነው።
ለምርቃት የበቃው የሚዲያ ኮምፕሌክስም ሀገራዊ ተልእኮውን በላቀ ብቃት እንዲወጣ የሚያስችለው ይሆናል።
የሚዲያ ኮምፕሌክሱ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ ሲሀን ሦስት ዘመናዊ የቴሌቪዥንና አራት የሬዲዮ ስቱዲዮዎችም አሉት።