የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም በተመረጡ ሰባት የፌዴራል ተቋማት ተግባራዊ ሊደረግ ነው

አዲስ አበባ ፤ጥር 22/2016 (ኢዜአ)፦ የመንግስት አገልግሎትና የአስተዳደር ማሻሻያ ሪፎርም በተመረጡ ሰባት የፌዴራል ተቋማት ላይ ተግባራዊ እንደሚደረግ ተገለጸ።

ይህ የተገለጸው የገንዘብ ሚኒስቴርና የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን በመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ማሻሻያ ሪፎርም ዙሪያ ባደረጉት  የምክክር መድረክ ላይ ነው።
 
በምክክር መድረኩ ላይ በመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ማሻሻያ ሪፎርም ይዘት፣ በመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ፖሊሲ፣ በመንግስት ሰራተኞች ብቃት ምዘና ማዕቀፍ እና በፖሊሲው ማስፈጸሚያ ዕቅድ ላይ ለገንዘብ ሚኒስቴርና እና ተጠሪ ተቋማት አመራሮች ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡

የሪፎርሙ ዓላማ የመንግስት ተቋማትን አደረጃጀትና አሰራር በማዘመን በክህሎትና በባህሪ የበቃ የሰው ኃይል አስተዳደርና ልማትን በመዘርጋት ለተገልጋዩ ኅብረተሰብ ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት በመስጠት የሀገርን የዕድገትና የልማት ግቦች አውን ለማድረግ እንደሆነ ተመላክቷል።

በመድረኩ ላይ የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነር ዶክተር መኩሪያ ኃይሌ ማሻሻያ ሪፎርሙ የገንዘብ ሚኒስቴርን ጨምሮ ለሙከራ በተመረጡ ሰባት የፌዴራል ተቋማት ላይ ተግባራዊ እንደሚደረግ ገልጸዋል።

ኮሚሽነሩ ሪፎርሙ የመንግስት ተቋማት አሰራራቸውን በማዘመን ለተገልጋዩ ኅብረተሰብ ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት ያስችላል ብለዋል።


 

የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ በበኩላቸው የገንዘብ ሚኒስቴር በመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ማሻሻያ ሪፎርሙ ለሙከራ ትግበራ አንዱ ሆኖ በመመረጡ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሪፎርሙን ማስፈጸም የሚችል የፕሮጀክት ጽህፈት ቤት በማደራጀት፣ በቂ ሃብት በመመደብ እና እቅድ በማውጣት በቶሎ ወደ ትግበራ እንደሚገባ አክለዋል።

የገንዘብ ሚኒስቴር ድኤታ ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ በበኩላቸው ትልልቅ ሀገራዊ ሪፎርሞችን መሸከም የሚችል ጠንካራ ሲቪል ሰርቪስ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ማሻሻያ ሪፎርም ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑን መግለጻቸውን ከገንዘብ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም