ኢዜአ ያስመረቀው የሚዲያ ኮምፕሌክስ ሀገራዊ መግባባትና ገጽታ ግንባታ ላይ እየሰራ ያለውን ስራ ይበልጥ ለማሳደግ አቅም የሚፈጥር ነው- ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ - ኢዜአ አማርኛ
ኢዜአ ያስመረቀው የሚዲያ ኮምፕሌክስ ሀገራዊ መግባባትና ገጽታ ግንባታ ላይ እየሰራ ያለውን ስራ ይበልጥ ለማሳደግ አቅም የሚፈጥር ነው- ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ
አዲስ አበባ ፤ጥር 22/2016 (ኢዜአ)፦ ኢዜአ ያስመረቀው የሚዲያ ኮምፕሌክስ በሀገራዊ መግባባትና ገጽታ ግንባታ ላይ እየሰራ ያለውን ስራ ይበልጥ ለማሳደግ አቅም የሚፈጥርለት እንደሆነ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ገለጹ።
ከተመሰረተ 82 ዓመታትን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ያስገነባውን ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስ ትናንት አስመርቋል።
የሚዲያ ኮምፕሌክሱ ዘመኑ የደረሰበትን የሚዲያ ቴክኖሎጂ ያሟላ ሲሆን ሦስት የቴሌቪዥንና አራት የሬዲዮ ዘመናዊ ስቱዲዮዎች አሉት።
በተጨማሪም ለቢሮ አገልግሎት የሚሆኑ ክፍሎች፣ የመሰብሰቢያ አዳራሾች ቤተመፅሐፍት፣ የመዝናኛ ማዕከልና ዘመናዊ ጂምናዝየም ያካተተ ነው።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ኢዜአ ያስመረቀውን የሚዲያ ኮምፕሌክስ ጎብኝተዋል።
ኢዜአ ያስመረቀው የሚዲያ ኮምፕሌክስ የሰራተኞችን የስራ ተነሳሽነት የሚያሳድግ እና ዓለም አቀፋዊ ተደራሽነቱን ለማስፋት የሚያስችል እንደሆነ ገልጸዋል።
ሚዲያ በሀገር ገጽታ ግንባታ ላይ የማይተካ ሚና እንዳለው ያነሱት ፕሮፌሰር መስፍን፣ በ82 ዓመታት ጉዞ ውስጥ ህዝብን በማስተማርና በማሳወቅ ትልቅ ሚና የነበረው ተቋም እንደሆነ ነው ያነሱት።
ከሀገራዊ መግባባት አኳያ በተለይም እሳቸው ከሚመሩት ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ስራዎችን ከመነሻው ጀምሮ ለህዝብ ተደራሽ በማድረግ የነበረውን አስተዋጽኦ አድንቀዋል።
ኢትዮጵያ የብዝሃ ማንነት ያላት ሀገር በመሆኗ እስከ ጠረፍ ያሉ ህዝቦች በቋንቋቸው ተደራሽ በመሆን እርስ በርስ እንዲተዋወቁና እንዲግባቡ ኢዜአ እያደረገ ያለውን ጥረት ይበልጥ መጠናከር እንዳለበት ገልጸዋል።