ቀጥታ፡

የኢዜአ ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስ ለሀገሪቷ የሚዲያ ኢንዱስትሪ እድገት አዲስ መሠረት የሚጥል ነው- የመገናኛ ብዙኃን አመራሮች

አዲስ አበባ ፤ ጥር 21/2016 (ኢዜአ)፦ የኢዜአ ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስ ለሀገሪቷ የሚዲያ ኢንዱስትሪ እድገት አዲስ መሠረት የሚጥል መሆኑን የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን አመራሮች ተናገሩ፡፡   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ያስገነባውን ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስ "ኢዜአ በአዲስ ምዕራፍ" በሚል መሪ ሀሳብ አስመርቋል። 

በምረቃ መርሃ-ግብሩ ላይ የተገኙት የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የሥራ ኃላፊዎች ኢዜአ በአዲስ ምዕራፍ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ታግዞ አስደናቂ የለውጥ ምዕራፍ ላይ መሆኑ የሚያስደስት ነው ብለዋል።  

በዛሬው እለት የተመረቀው ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስ በአፍሪካ ግንባር ቀደም የዜና ተቋም ለመሆን የሰነቀውን ራዕይ ለማሳካት የሚያግዝ መሆኑን ገልፀዋል።

ከአርትስ ቴሌቪዥን የመጡት  አቶ መላኩ ብርሃኑ፤ የሚዲያ ኮምፕሌክሱ በአፍሪካ ተምሳሌት፣ አስተማማኝና ተፅዕኖ ፈጣሪ የዜና ምንጭ የመሆን ራዕዩን ለማሳካት ትልቅ አቅም እንደሚሆን ተናግረዋል። 

ለሀገሪቷ የሚዲያ ኢንዱስትሪ እድገት አዲስ መሠረት የሚጥል የተሟላ የሚዲያ ኮምፕሌክስ ስለመሆኑም አንስተዋል።


 

የአሐዱ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ዋና ሥራ አስኪያጅ ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ፤ ኢዜአ ለአፍሪካ የነፃነት ትግል የላቀ አስተዋፅዖ ያበረከተ አንጋፋ አህጉራዊ የሚዲያ ተቋም መሆኑን ገልፀዋል። 

አሁን ላይ ደግሞ በአዲስ ምዕራፍ እያደረገ ያለው አዲስ የስኬት ጉዞ የሚደነቅ ጅማሮ መሆኑን ጠቅሰዋል።  


 

የአሻም ቴሌቪዥን ሥራ አስኪያጅ ጌታሁን ንጋቱ፤ ኢዜአ የገነባቸው የሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ስቱዲዮዎች የይዘት ሥራዎችን በጥራት እና በፍጥነት ለመሥራት የሚያግዙ መሆኑን ገልፀዋል። 

የኢዜአ የሚዲያ ኮምፕሌክስ ዘመኑ የደረሰበትን የሚዲያ ቴክኖሎጂ ያሟላ ሲሆን፤ ሦስት የቴሌቪዥንና አራት የሬዲዮ ዘመናዊ ስቱዲዮችን አካቷል።  

ከተመሠረተ 82 ዓመታትን ያስቆጠረው ኢዜአ ብሔራዊ መግባባት የመፍጠርና የሀገር ገፅታ ግንባታ ተልዕኮውን ለማሳካት ዜና እና ዜና ነክ መረጃዎችን ተደራሽ በማድረግ ላይ ይገኛል።

ኢዜአ በ2022 በአፍሪካ ተምሳሌት፣ አስተማማኝና ተፅዕኖ ፈጣሪ የዜና ምንጭ የመሆን ራዕዩን ለማሳካት በላቀ ብቃት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።

የሥርጭትና ተደራሽነት አድማሱን በምስራቅ አፍሪካ ለማስፋት በኬንያና በጂቡቲ ቅርንጫፎችን ለመክፈት በዝግጅት ላይ ይገኛል።

ኢዜአ በ1934 ዓ.ም በወቅቱ የጽሕፈት ሚኒስቴር ተብሎ ይጠራ በነበረው ተቋም፣ የጋዜጣ እና ማስታወቂያ ጽህፈት ቤት ሥር እንደ አንድ የሥራ ክፍል መቋቋሙ ይታወሳል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም