ቀጥታ፡

"ፀሐይ" አውሮፕላን

ዛሬ የጣልያን መንግሥት "ፀሐይ"ን ለኢትዮጵያ መንግሥት ያስረከቡበት የታሪካዊ ሁነት ቀን ሆኗል።

 "ፀሐይ" በ1935 ዓ.ም ሄር ሉድዊግ ዌበር የተባለው ጀርመናዊ ኢንጂነር እና የንጉሱ ፓይለት በወቅቱ ከነበሩ ኢትዮጵያዊያን ጋር በመሆን በኢትዮጵያ የተሰራ የመጀመሪያው አውሮፕላን መሆኑንና ስያሜውም የቀዳማዊ ኃይለስላሴን ልጅ ልዕልት ፀሐይን ለማሰብ የተሰጠ እንደነበር ተመላክቷል።
 
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ላለፈው አንድ አመት ጊዜ ከጣልያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጂኦርጂያ ሜሎኔ ጋር አውሮፕላኑ ወደ ኢትዮጵያ ስለሚመለስበት ሁኔታ ትልቅ ጥረት እና ሰፊ ንግግር ሲያደርጉ መቆየታቸውም ተገልጿል።

ፀሐይ ባለሁለት መቀመጫ እና ሁለትዮሻዊ መቆጣጠሪያ ያለው ብሎም የባለከፍተኛ ኃይል ሞተር ባለቤት ተደርጎ የተሰራ አውሮፕላን እንደነበርም የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መረጃ ያመላክታል።

 "ፀሐይ" ኮምፓስ፣ የአብራሪ መቆጣጠሪያዎች፣ ሁለት ያለ ፍሬን ማቆሚያ የተገጠሙ የማረፊያ ሽክርክሪቶች የነበሩትም ነበር። 

ሞተሩ ባለሰባት ሲሊንደር ዋልተር ቪነስ ሲሆን የውሃ ማቀዝቀዣ ስርዓት የነበረው የ115 የፈረስ ጉልበት ባለቤትም እንደነበር በመረጃው ተጠቅሷል።

"ፀሐይ" ከሁለተኛው የአለም ጦርነት በፊት በኢትዮጵያ የተሰራ ብቸኛ አውሮፕላን ነው።

 ፀሐይ በውስን ሃብት እና ስፍራ በጊዜው የነበሩትን አናፂዎች እውቀት እና የእጅ ጥበብ በመጠቀም የተሰራ አውሮፕላን ሲሆን የ1930ዎቹ የአቪየሽን ጥረት ማሳያ ሆኖ የተረፈን አውሮፕላን  መሆኑም ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም