ቀጥታ፡

ኢዜአ በአፍሪካ ተምሳሌት  አስተማማኝና ተጽዕኖ ፈጣሪ የዜና ምንጭ ለመሆን ለሚያደርገው ጥረት መሳካት አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል

አዲስ አበባ ፤ ጥር 21/2016 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) በአፍሪካ ተምሳሌት፣ አስተማማኝና ተጽዕኖ ፈጣሪ የዜና ምንጭ ለመሆን የሚያደርገው ጥረት እንዲሳካ አስፈላጊው ክትትልና ድጋፍ የሚደረግ መሆኑን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ያስገነባውን ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስ "ኢዜአ በአዲስ ምዕራፍ" በሚል መሪ ሃሳብ አስመርቋል።


 

ኢዜአ በአገር ውስጥና በውጭ አገራት ዋነኛ የዜና ምንጭ በመሆን ብሔራዊ መግባባትን የመፍጠርና የአገር ገጽታ የመገንባት ተልዕኮ ይዞ የሚሰራ ታላቅ ተቋም መሆኑ ይታወቃል።

በ82 የአገልግሎት ዘመኑ በአገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና የኢኮኖሚ ልማት ስኬቶች የራሱን አሻራ እያሳረፈም ቀጥሏል።

አሁን ላይ ደግሞ በአዲስ ምእራፍ አዲስ የሚዲያ ኮምፕሌክስ በመገንባት ተልእኮውን ለማሳካት እየሰራ ይገኛል።

በሚዲያ ኮምፕሌክሱ የምረቃ-ስነ-ስርዓት ላይ የተገኙት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እውነቱ አለነ እና የቋሚ ኮሚቴው አባል አቡኔ አለም፤ ኢዜአ በየጊዜው አቅሙን ለማጎልበትና የተሻሉ የይዘት ስራዎችን ለማውጣት እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀዋል።


 

ኢዜአ በአፍሪካ ተምሳሌት፣ አስተማማኝና ተጽዕኖ ፈጣሪ የዜና ምንጭ ለመሆን የሚያደርገው ጥረት እንዲሳካ ምክር ቤቱ አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

ዓለም አቀፍ ተደራሽነትና ተወዳዳሪነቱን የበለጠ ለማሳደግ የቋንቋ ስብጥሩን ማስፋቱንም አድንቀው አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።

አንጋፋው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ብሔራዊ መግባባት የመፍጠርና የሀገር ገፅታ ግንባታ ተልዕኮውን ለማሳካት ዜና እና ዜና ነክ መረጃዎችን ተደራሽ በማድረግ ላይ ይገኛል።

በመላ ሀገሪቱ 38 ቅርንጫፎችን በመክፈት በቅርቡ የጀመራቸውን ሶማሊኛ እና አፋርኛን ጨምሮ በአማርኛ፣ በአፋን ኦሮሞና በትግርኛ ቋንቋዎች አስተማማኝ የዜና ምንጭ ሆኖ ቀጥሏል።

በእንግሊዝኛ፣ በአረብኛ እና በፈረንሳይኛ ቋንቋዎችም የኢትዮጵያን ገፅታና እውነታ ለዓለም ተደራሽ እያደረገ ነው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም