ቀጥታ፡

ኢዜአ አገራዊ መግባባትን በመፍጠርና ህብረ-ብሄራዊ አንድነትን በማጠናከር በኩል ትልቅ አበርክቶ አለው-የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ ፤ ጥር 21/2016 (ኢዜአ)፦ኢዜአ በኢትዮጵያ አገራዊ መግባባትን በመፍጠርና ህብረ-ብሄራዊ አንድነትን በማጠናከር በኩል ትልቅ አበርክቶ እንዳለው የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።

በምረቃ-ስነስርዓቱ ላይ የተገኙት የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ፤ ተቋሙ ከመሰረተ ልማት ግንባታ ጀምሮ በቴክኖሎጂና በሰው ሃይል ራሱን ለማብቃት የሄደበትን ርቀት አድንቀዋል።

''የጋዜጠኝነት ስራ ህይወት ነው'' ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ በየትኛውም ሁኔታ ስራ መስራት የሚያስችል ምቹ ከባቢ መፍጠር ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህ ረገድ ኢዜአ ለሰራተኞች ምቹ የስራ ከባቢ ከመፍጠር አኳያ የሰራቸው ስራዎች ለሌሎች ተሞክሮ ሊሆን የሚችል ነው ብለዋል።

 ኢዜአ የተጣለበትን ሃላፊነት በብቃት እንዲወጣ ተቋማቸው አስፈላጊውን ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑንም ሚኒስትር ዴኤታዋ ሰላማዊት ካሳ ገልጸዋል።


 

የመንግስት ኮሙኒኬሽን ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ዴሲሳ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በተቋም ግንባታ የረጅም ጊዜ ታሪክ ያላት መሆኑን ከምናሳይባቸው ተቋማት አንዱ ኢዜአ ነው ብለዋል።

ተቋሙ ኢትዮጵያውያንን እርስ በእርስ ከማስተዋወቅ ባለፈ አስተማማኝ መረጃዎች ለህዝቡ ተደራሽ እንዲሆን እየሰራ ያለው ስራ የሚያኮራ ነው አስረድተዋል።

ኢዜአ በተለይም የተሻሉ የይዘት ስራዎች ላይ ትኩረት በማድረግ የኢትዮጵያን ሃብቶች በማስተዋወቅና የአገር ገጽታን በመገንባት ረገድ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ መስራት አለበት ሲሉ ሚኒስትር ዴኤታው ከበደ ዴሲሳ ተናግረዋል።


 

ከተመሠረተ 82 ዓመታት የሆነው አንጋፋው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ብሔራዊ መግባባት የመፍጠርና የሀገር ገፅታ ግንባታ ተልዕኮውን ለማሳካት ዜና እና ዜና ነክ መረጃዎችን ተደራሽ በማድረግ ላይ ይገኛል።

ለዚህም በመላው ሀገሪቱ 38 ቅርንጫፎችን በመክፈት በቅርቡ የጀመራቸውን ሶማሊኛ እና አፋርኛ ጨምሮ በአማርኛ፣ በአፋን ኦሮሞና በትግርኛ ቋንቋዎች ዜናና ዜና ነክ መረጃዎችን እያቀረበ ይገኛል።

በእንግሊዝኛ፣ በአረብኛ እና በፈረንሳይኛ ቋንቋዎችም የኢትዮጵያን አሁናዊ ገፅታና እውነታ ለዓለምአቀፉ ማህበረሰብ ተደራሽ እያደረገ ነው።

ኢዜአ በ2022 በአፍሪካ ተምሳሌት፣ አስተማማኝና ተጽዕኖ ፈጣሪ የዜና ምንጭ የመሆን ራዕዩን ለማሳካት በላቀ ብቃት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም