ኢዜአ በአዲስ ምእራፍ ወደ ስራ መግባቱ ለብሄራዊ መግባባትና ለሀገር ገጽታ ግንባታ ያለውን ሚና ይበልጥ የሚያጠናክር ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢዜአ በአዲስ ምእራፍ ወደ ስራ መግባቱ ለብሄራዊ መግባባትና ለሀገር ገጽታ ግንባታ ያለውን ሚና ይበልጥ የሚያጠናክር ነው
አዲስ አበባ ፤ ጥር 21/2016 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) በአዲስ ምእራፍ በዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስ ወደ ስራ መግባቱ ለብሄራዊ መግባባትና ለሀገር ገጽታ ግንባታ እያበረከተ ያለውን ሚና ይበልጥ የሚያጠናክር መሆኑን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር መሀመድ እድሪስ ገለጹ።
ከተመሠረተ 82 ዓመታትን የተሻገረው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ያስገነባውን ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት አስመርቋል።
በምረቃ መረሃ-ግብሩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር መሀመድ እድሪስ፤ ኢዜአ ለኢትዮጵያ ሚዲያዎች የጀርባ አጥንት ሆኖ ረዥም ዘመናትን የዘለቀ ተቋም መሆኑን ገልጸዋል።
ከሁሉም የሀገሪቷ አቅጣጫዎች መረጃዎችን ተደራሽ ማድረጉ እንዳለ ሆኖ በሀገር ገጽታ ግንባታና የሀገረ መንግስት ግንባታ ሂደት የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል።
አዲስ ያስገነባው ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስም ሀገራዊ ተልዕኮውን በብቃት ለመወጣት የሚያስችለው መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አሁን የደረሰበት ደረጃ በሚዲያ ኢንዳስትሪው አዲስ የምስራች መሆኑንም ነው የተናገሩት።
ኢዜአ በአዲስ ምእራፍ በከፍታ ወደ ስራ መግባቱ በሁሉም መስክ በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ላሉ ስራዎች ሁነኛ አጋዥ እንደሚሆንም ነው የገለጹት።
ኢዜአ በ2022 በአፍሪካ ተምሳሌት፣ አስተማማኝና ተጽዕኖ ፈጣሪ የዜና ምንጭ የመሆን ራዕዩን ለማሳካት በላቀ ብቃት እየተንቀሳቀሰ መሆኑ ይታወቃል።
የስርጭትና ተደራሽነት አድማሱን በምስራቅ አፍሪካ ለማስፋት በኬንያ እና በጅቡቲ ቅርንጫፎችን ለመክፈትም በዝግጅት ላይ ይገኛል።