አንጋፋው አህጉራዊ ዜና አገልግሎት፣ ብቸኛው ሀገራዊ የዜና ወኪል- 'ኢዜአ'

(በአየለ ያረጋል)

'ኢዜአ ዘግቧል' የምትለዋ ሐረግ ለሀገሬው ተደራሲያን ጆሮ እንግዳ አይደለችም። ዳሩ ግን ስለ 'ዜና አገልግሎት' ተቋማዊ ሚና ዛሬም ግር የሚሰኙ በርካታ ናቸው። የዜና አገልግሎት ስራዎች ከሌሎች መገናኛ ብዙሃን ጀርባ እንጂ ፊት ለፊት ስለማይታዩ ስለምንነቱና ግብሩ በቅጡ ካለመረዳት የመነጨ ነው። 

ዜና አገልግሎቶች ከዓለማችን ሁነኛ የመገናኛ ብዙሀን አይነቶች መካከል ይጠቀሳሉ። የራሳቸው የተለየ መልክና ቅርፅ አላቸው። ዜና አገልግሎት ተቋማት ‘የዜና ምንጮች’ በሚልም ይጠራሉ። በእንግልጣር ቋንቋ “Newswires, News Services, News Agencies’ ይሰኛሉ። 

ለሁሉም አይነት መገናኛ ብዙሃን ዘውጎች መረጃ መጋቢዎች ናቸው። በቀላል ምሳሌ ጋዜጦች፣ መፅሔቶች፣ ሬዲዮና ቴሌቪዥንና መሰል መገናኛ ብዙሃን የመረጃ ቸርቻሪ ከሆኑ ዜና አገልግሎት ደግሞ የመረጃ አምራች እና ጅምላ አከፋፋይ ናቸው ማለት ነው።

ስለዚህ ዜና አገልግሎቶች የዜናና የመረጃ ማዕድ ቤቶች ናቸው። አደረጃጀትና ሕጋዊ ድንጋጌያቸው እንደየሃገሩ ልዩ መልክና ባህሪ ቢለያይም በተግባር ግን ዜና እና ዜና ነክ መረጃዎችን በማምረት ተመሳሳይ ናቸው። ይሄውም ወቅታዊ መረጃን በማጠናቀር መረጃ ለመግዛት ለተዋዋሏቸው የህትመት እና ብሮድካስት ሚዲያ ተቋማት ደንበኞች እንዲሁም በራሳቸው አማራጭ ለህዝቡ ተደራሽ ያደርጋሉ።

በአህጉራዊ፣ ብሔራዊ እና ድንበር ዘለልነት ይደራጃሉ። ከሀገር ሀገር መረጃ የማሸጋገር፣ ከመላው የዓለም ዙሪያ በተናጠል መረጃ መሰብሰብ ለማይችሉ ሚዲያዎች ዘገባዎችን በማሰናዳት የማድረስ፣ የውጭ ዜና አከፋፋይነት እና የሰበር ዜና ባለሟልነት ሚና አላቸው።

የዜና ምንጮች ዛሬም ፈጣን፣ ለ24/7 ሰዓታት ፍሰት የማያቋርጡና በዳራ መረጃ ቋቶች ባለቤት በመሆናቸው ለነባር እና አዳዲስ ሚዲያ ተቋማት (conventional and online) ሕልውና የጀርባ አጥንት ናቸው። ለዚህ ነው ‘ድምጽ አልባ የመገናኛ ብዙሃን የጀርባ አጥንት’ የሚሰኙት።

በዓለም ላይ ቀዳሚው የዜና ምንጭ ተቋም ዝነኛው የፈረንሳዩ ዜና አገልግሎት ወይም አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ (AFP) ነው። በአውሮፓዎያን ዘመን ቀመር 1835 ቻርለስ ሃቫስ (charles havas) የተባለ ፈረንሳዊ ዜጋ የ’ሃቫስ ኤጀንሲ’ በሚል ያቋቋመው የመረጃ መሸጫ ሱቅ ለዜና አገልግሎት መወለድ ምክንያት ነው። በቴሌግራፍ ሲስተም እያደገ፣ ደንበኞቹን እያበዛ ሄዶ በመጨረሻም የዛሬው አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ስም ይዞ ተመሰርቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አጀማመር አመክንዮ 

በ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ከአዕምሮ ጋዜጣ የጀመረው የኢትዮጵያ ዘመናዊ መገናኛ ብዙሀን ታሪክ እስከ ፋሺስት ኢጣሊያ  ወረራ ድረስ ሬዲዮ እስከ መክፈት እምርታ አሳይቷል። 

የፋሺስት ወረራ ተቀልብሶ ኢትዮጵያ ድል ባደረገች ማግስት የሕትመትና የብሮድካስት (ሬዲዮ) መገናኛ ብዙሃን መቋቋም ጀመሩ። ዳሩ እነዚህን መገናኛ ብዙሀን በመረጃ የሚቀልብ የዜና አገልግሎት ተቋም ማቋቋም ግድ ሆነ። በዚህም በ1934 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ ‘አዣንስ ዳሤክሲዮን’ በሚል የዜና አገልግሎት ተቋም ተመሰረተ። ይሄውም የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ከተመሰረተ መቶ ዓመታት በኋላ ማለት ነው። 

ይህ ወቅት ሁሉም የአፍሪካ ሀገራት በቅኝ ግዛት ቀንበር ስር የነበሩበት ዘመን ነበር። በዚህም ደቡብ አፍሪካን በመሰሉ ጥቂት ሀገራት በቅኝ ገዥዎች ከተቋቋሙ ውስን የዜና አገልግሎት አማራጮች በስተቀር ማንም ሀገር የዜና አገልግሎት የማቋቋም ዕድሉ አልነበረውም። ስለዚህ ኢትዮጵያ የራሷን ሀገር በቀል የዜና አገልግሎት በመመስረት ቀዳሚዋ አፍሪካዊት ሀገር ያደርጋታል። ኢዜአ ዘንድሮ 82 ዕድሜ ያስቆጠረ የአፍሪካ አንጋፋ ዜና አገልግሎት ተቋም ሆኗል።

ኢትዮጰያ ዜና አገልግሎት በዘመናት መካከል

ቀዳማዊ አጼ ኅይለስላሴ ሚያዝያ 10 ቀን 1959 ተቋሙን በጎበኙበት ወቅት “የኢትዮጵያ የወሬ ምንጭ ወኪሎች ስታባሉ ምንጭና ኩሬ የተለያዬ መሆኑን ማወቅ አለባችሁ። ምንጭ የማያቋርጥ፣ ኩሬ ግን የሚደርቅ ነው” ያሉትም የዜና አገልግሎት በዘመናት መካከል የማይነጥፍ የመረጃ ምንጭነቱን ለመግለጥ ይመስላል።

ኢዜአ ከተቋቋመበት ዕለት ጀምሮ ስያሜውን፣ የተደራሽነት አድማሱን እና አደረጃጅቱን እየለወጠ የመጣ አንጋፋ ተቋም ነው። ከበርካታ የአፍሪካ ሀገራት ዜና አገልግሎት ተቋማት በተሻለ መንገድ ተቋማዊ ቀጣይነቱን ይዞ የዘለቀ ተቋም እንደሆነ የሚናገሩ የዘርፉ ምሁራንም አሉ።

በ1934 ዓ.ም በያኔው ጽህፈት ሚኒስቴር የፕሬስ ክፍል ውስጥ ነበር የተቋቋመው። በ1936 ዓ.ም ‘አዣንስ ዳይሬክሲዮን’ የሚል ስያሜ ያዘ። ከ1940-1946 ባሉ ዓመታት ግን በባጀት እጥረት ተዘግቶ እንደነበር ታሪክ ይነግረናል። 

በ1957 ዓ.ም ድርጅቱ ‘የኢትዮጵያ የወሬ ምንጭ’ የሚል ስም ይዞ ቀጠለ። የዛሬውን ‘የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት’ የሚል ስያሜ ያገኘው በ1960 ዓ.ም ነበር። ይሄውም ንጉሠ ነገሥቱ በወቅቱ ኢዜአን በጎበኙበት ወቅት ‘ወሬ’ የሚለው ቃል እንዲለወጥ በማሳሰባቸው እንደሆነ ይነገራል። በዚህም ዕውቁ ጋዜጠኛ እና የዘመናዊ ጋዜጠኝነት አባት የሚሰኘው ነጋሽ ገብረማርያም ‘ዜና አገልግሎት’ የሚለውን ስያሜ እንዳወጡት በወቅቱ የተቋሙ ስራ አስኪያጅ የነበሩት አምባሳደር ዘውዴ ረታ በአንድ ወቅት ገልጸው ነበር።

በ1970 ዓ.ም በማስታወቂያ ሚኒስቴር በመምሪያ ደረጃ ተዋቀረ። የቴክኒክና ኦፕሬሽን፣ የአዲስ አበባ ዜና ዝግጅትና የክፍለ ሀገራት ዜና ዝግጅት፣ የውጭ ቋንቋዎች ዜና ዝግጅት የተባሉ አራት ክፍሎች ነበሩት። 

ኢዜአ በ1987 በአዲስ አዋጅ ራሱን የሚያስተዳድር ተቋም እንዲሆን የተደነገገ ሲሆን በ1990 ዓ.ም ራሱን ማዘመን (ሞደርናይዜሽን) ፕሮጀክት ተግብሯል። ከአውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ከከ1991 እስከ 2000 ዓ.ም ባሉት ዓመታት ኢዜአ የተሻለ እምርታ ያመጣበት፣ የተሻለ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ የሆነበት እንዲሁም በክልል ቅርንጫፎችን ያሰፋበት እና የራሱን ህንጻዎች የገነባበት ወርቃማ ጊዜ እንደነበር ይነሳል። የቀድሞው የኢዜአ ስራ አስኪያጅ አምባሳደር ዘውዴ ረታ በወቅቱ የኢዜአን የማዘመኛ ፕሮጀክት ‘ታላቅ እምርታ’ ሲሉ ያሞካሹትም ለዚህ ይመስላል።

በ2001 ዓ.ም በመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ፅህፈት ቤት ሲቋቋም ግን ኢዜአ የተቋሙ አንድ የስራ ክፍል ሆኖ በዳይሬክትሬት እንዲመራ ተወሰነ። ይህም በ1990ዎቹ የጀመረውን ራሱን የማዘመን ፕሮጀክት ወደኋላ የመለሰ ነበር።

በ2006 ዓ.ም ደግሞ ‘የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ኤጀንሲ’ ተብሎ ዳግም ራሱን ችሎ ተቋቋመ። በ2011 ዓ.ም ተጠሪነቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሆኖ ዳግም ተደራጅቷል። ኢዜአ የ10 ዓመታት ፍኖተ ካርታ በመቅረፅ ሪፎርሞችን እያካሄደ እና ተቋማዊ አስቻይ የሕግ ማዕቀፎችን እያሻሻለ በለውጥ ጎዳና ላይ ይገኛል።

‘አስተማማኝ የዜና ምንጭ’ የሚል መለያ የሚጠቀመው ኢዜአ በአሁኑ ወቅት በመላ ኢትዮጵያ 38 ቅርንጫፎች አሉት። እስካሁን አማርኛ፣ አፋን ኦሮሞ፣ ትግርኛ፣ ሶማሊኛ እና አፋርኛ የሀገር ውስጥ ቋንቋዎች እንዲሁም እንግሊዝኛ፣ አረብኛና ፈረንሳይኛ ቋንቋዎች ስራዎቹን ተደራሽ እያደረገ ይገኛል። ይህም የኢትዮጵያን መልክ እና ልክ በቅጡ ለመንገር፣ የሀገር ገፅታና ሐቅ ለዓለም ተደራሽ ለማድረግ ያስችለዋል።

ኢዜአ በዜናና ዜና ነክ፣ በፎቶና በዘጋቢ ፊልም፣ በሕትመት፣ በስልጠናና ማማከር ስራዎች የተደራሽነቱን አድማሱን እያሰፋ ይገኛል። አንጋፋነቱን በሚመጥኑ እና ለፖለሲ አውጪዎች ግብዓት የሚሆኑ ሃሳቦች የሚንሸራሸርባቸው ቁልፍ አገራዊ አጀንዳዎች ዙሪያ አይነተ ብዙ መድረኮችን እያዘጋጀ ነው።

መገናኛ ብዙሃን ከኢንተርኔት ቴክኖሎጂ መፈጠር ማግስት አዲስ የመረጃ ምንጭ አማራጭ ቢያገኙም ቅሉ የዜና አገልግሎት አስፈላጊነት ግን የሚገታ አይደለም። በተለይም ገጠራማ ማህበረሰብ በሚበዛባት ኢትዮጵያ ሀገር አቀፍ ሁነቶችን በተደራጀ እና ወቅቱን በዋጀ አግባብ በማጠናቀር የሚቀርቡ መረጃዎች ለመገናኛ ብዙሃን አይነተኛ ቀለብ ሆነው እንደሚቀጥሉ ዕሙን ነው።

ኢዜአ በአዲስ ምዕራፍ

ኢዜአ “በአፍሪካ ተምሳሌት፣ አስተማማኝና ተጽዕኖ ፈጣሪ የዜና ምንጭ መሆን” የሚል ራዕይ ሰንቋል። ራዕዩን ዕውን ለማድረግ ደግሞ “በኢትዮጵያና በህዝቦቿ ጥቅም ላይ ያተኮሩ አገራዊና ዓለምአቀፍ ዜና እና ዜና ነክ ዘገባዎችን እንዲሁም ፕሮግራሞችን በማሰራጨት በአገር ውስጥና በውጭ ዋነኛ የዜና ምንጭ በመሆን፤ ብሔራዊ መግባባት መፍጠርና አገራዊ ገጽታን መገንባት” የሚል ተልዕኮ አንግቦ እየተንቀሳቀሰ ነው። 

አንጋፋው የዜና ምንጭ ባለፉት ዓመታት ሲያስገነባ የቆየውን የሚዲያ ኮምፕሌክስ ዛሬ አስመርቋል። የሚዲያ ኮምፕሌክሱ የዘመኑ የሚዲያ ቴክኖሎጂ የተገጠመለት፣ ሶስት የቴሌቪዥንና አራት የሬዲዮ ዘመናዊ ስቱዲዮዎች ያቀፈ እንዲሁም ለቢሮ አገልግሎት ክፍሎች፣ የመሰብሰቢያ አዳራሾች፣ ቤተ-መፃሕፍት፣ የስፖርተና መዝናኛ ክፍሎችን  ያካተተ ነው። 

ሚዲያ ኮምፕሌክሱ ኢዜአ በአዲስ ምዕራፍ ለመከወን የያዛቸውን ግቦችንና ተልዕኮዎች ዕውን ለማድረግ ያስችለዋል። ብሔራዊ መግባባት የመፍጠርና የሀገር ገፅታ ግንባታ ተልዕኮውን ለማሳካት ዜና እና ዜና ነክ መረጃዎችን ተደራሽ በማድረግ ላይ ይገኛል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም