በመንግሥትና የግል አጋርነት ማዕቀፍ 60 ሺህ ቤቶች ለመገንባት ዝግጅት መጠናቀቁን የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
በመንግሥትና የግል አጋርነት ማዕቀፍ 60 ሺህ ቤቶች ለመገንባት ዝግጅት መጠናቀቁን የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ
አዲስ አበባ ፤ ጥር 21/2016 (ኢዜአ)፦በአዲስ አበባ በመንግሥትና የግል አጋርነት ማዕቀፍ 60 ሺህ ቤቶች ለመገንባት ዝግጅት መጠናቀቁን የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 12ኛ መደበኛ ስብሰባውን ያካሄደ ሲሆን ምክር ቤቱ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴርን የ6 ወራት በጀት አፈጻጸም አዳምጧል።
በዚሁ ጊዜ የምክር ቤቱ አባላት በቤት አቅርቦትና በመንገድ መሰረተ ልማት ዝርጋታ ዙሪያ ሚኒስቴሩ የሚከተላቸውን ዘመናዊ አሰራሮች በተመለከተ ጥያቄ አንስተው ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል።
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ በሰጡት ማብራሪያ በ2016 ግማሽ ዓመት 4 ሺህ ቤቶችን ለመገንባት ታቅዶ 3 ሺህ 647 የመንግሥት ኪራይ ቤቶች መገንባታቸውን ተናግረዋል።
ሚኒስቴሩ ባለፉት ስድስት ወራት በአዲስ አበባ 3 ሺህ 500፣ በአማራ 543፣ በኦሮሚያ 2 ሺህ 398 ፣በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ 153፣ በሲዳማ 45፣ በድሬዳዋ 358 ቤቶች በድምሩ 6 ሺ 988 ቤቶች በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ዜጎች ተላልፏል ብለዋል።
የግሉን ዘርፍ በማሳተፍ የቤት አቅርቦትን የማሻሻል ጉዳይ ትኩረት የተሰጠው ሲሆን በ2016 በጀት ግማሽ ዓመት ብቻ 82 ሺህ 500 ቤቶች ግንባታ ለማከናወን ታቅዶ 75 ሺህ 199 ቤቶችን መገንባት ተችሏል።
ከዚህ በተጨማሪ በመንግሥትና የግል አጋርነት ማዕቀፍ በአዲስ አበባ 60 ሺህ መኖሪያ ቤቶች ለመገንባት ዝግጅት መጠናቀቁን ሚኒስትሯ አሳውቀዋል።
ለቤቶቹ ግንባታ መንግሥት የለማ መሬት የሚያቀርብ ሲሆን ባለኃብቶች ፋይናንስና ቴክኖሎጂ በማቅረብ የቤቶቹ ግንባታ እንደሚከናወንም አብራርተዋል።
ከዚህ ቀደም በ40/60 እና 20/80 ተመዝግበው ቤት ለማግኘት የሚጠባበቁ ነዋሪዎችን ፍላጎት ለማሟላት የህብረት ስራ ማህበራት እንዲደራጁ የሚያስችል መመሪያ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።
በመመሪያው መሰረት 54 ማህበራት እንደተደራጁ ጠቁመው መሬት ቀርቦላቸው ወደ ግንባታ ለመግባት ዝግጅት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ከመንገድ መሰረተ ልማት ዝርጋታ ጋር በተያያዘ ሚኒስትሯ በሰጡት ማብራሪያ በግማሽ ዓመቱ በ50 ፕሮጀክቶች የተያዙ 122 ኪሎ ሜትር መንገዶች ላይ ከባድ ጥገና ለማካሄድ ታቅዶ 85 ኪሎ ሜትር ጥገና ተከናውኗል ነው ያሉት።
ከዚህ ባለፈም ነባር መንገዶችን የማጠናከር ፣ደረጃቸውን የማሻሻልና አዲስ የመንገድ ግንባታ ተግባራት መከናወናቸውን አስረድተዋል።
ወይዘሮ ጫልቱ እንዳሉት በጥቅሉ የመንገድ መሰረተ ልማት ሽፋኑን ለማሳደግ በተሰሩ ሥራዎች የመንገድ ሽፋኑን ወደ 169 ሺህ 450 ኪሎ ሜትር ማሳደግ ተችሏል።