ቀጥታ፡

የአረንጓዴ አሻራ ልማት የብዝኃ-ሕይወት ኃብቶች እንዲጠበቁ ጉልህ ሚና እየተወጣ ነው

አዲስ አበባ ፤ ጥር 21/2016 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የብዝኃ-ሕይወት ኃብቶች እንዲጠበቁና እንዲሰፉ ጉልህ አስተዋፅዖ እያበረከተ መሆኑን የኢትዮጵያ ብዝኃ-ሕይወት ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ብዝኃ-ሕይወት ሁሉንም ሥነ-ሕይወታዊ ኃብቶች፣ እፅዋት፣ እንስሳትና ደቂቅ አካላት እንዲሁም በውስጣቸው የያዟቸው ዘረ-መሎችና የሚፈጥሯቸውን ውህዶች የሚያካትት ነው። 

ኢትዮጵያም ከፍተኛ የብዝኃ-ሕይወት ኃብት ካላቸው አገራት መካከል ትጠቀሳለች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በ2011 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብርን ያስጀመሩ ሲሆን በአምስት ዓመታትም ከ32 ቢሊየን በላይ ችግኞች ተተክሏል።

በ2015 ዓ.ም በተጀመረው ሁለተኛው ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ለጥምር ደንና ለአገር በቀል እጽዋቶች ትኩረት ተሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ብዝኃ-ሕይወት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መለሰ ማርዮ፤ አረንጓዴ አሻራ ለብዝኃ- ሕይወት ጥበቃ ሥራ ያለው ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን ገልፀዋል።

በዚሁ የልማት መርሃ-ግብር የደን ሽፋን በመጨመሩ የእጽዋትና እንስሳት ኃብት እንዲጠበቅ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለዱር እንስሳት ጥበቃም አስተዋፅዖ እያደረገ ነው ብለዋል።

በተለያዩ ምክንያቶች ጉዳት የደረሰባቸው የብዝኃ-ሕይወት ኃብቶች መልሰው እንዲያገግሙ ከማድረግ ባለፈ ዝርያዎች፣ እጽዋት፣ እንስሳትና ደቂቅ አካላት በቁጥር እንዲጨምሩ እያደረገ እንደሚገኝ ነው ዶክተር መለሰ የገለጹት።

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ታኅሣሥ ወር 2022 በካናዳ በተካሄደው 15ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የብዝኃ-ሕይወት ጉባዔ (ኮፕ-15) ዓለም አቀፍ የብዝኃ-ሕይወት ማዕቀፍ ስምምነት ጸድቋል።

ስምምነቱ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2050 የሚሳኩ አራት ግቦች እና እ.አ.አ በ2030 እውን ለማድረግ የታሰቡ 23 ዒላማዎች በውስጡ ይዟል።

የአረንጓዴ አሻራ ልማቱ ኢትዮጵያ በስምምነቱ ከተቀመጡ 23 ዒላማዎች መካከል በቀጥታ ግማሽና ከዚያ በላይ ማሳካት የሚያስችል ነው።  

የሥርዓተ-ምህዳር ትስስርን ማጠናከር፣ የብዝኃ-ሕይወት መልሶ ማገገም፣ ጥብቅ አካባቢዎችን ማስፋት፣ ሕይወታዊ ኃብቶች እንዳይጠፉ መጠበቅ፣ የእጽዋትና የዱር እንስሳት ጥበቃ፣ የመጤ ወራሪ ዝርያዎች መስፋፋትና የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን መቀነስ ከተቀመጡት የትኩረት አቅጣጫዎች የሚጠቀሱ ናቸው ብለዋል።

የአረንጓዴ አሻራ በስምምነቱ በቀጥታ ቁርኝት ካላቸው የስምምነቱ ዒላማዎች ባሻገር ሌሎች የተቀመጡ ጉዳዮች ጋር ቀጥታ ባልሆነ መንገድ ትስስር እንዳለውም ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ ከሚገኙ የብዝኃ-ሕይወት ኃብቶች በአብዛኛው በደን ውስጥ እንደሚገኙ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ከዚህ አኳያ የአረንጓዴ አሻራ ልማት ላይ እያበረከተ ያለው አስተዋፅዖ ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ ለግብርና ምርት ያሏትን የተለያዩ ምቹ የአየር ንብረት ዓይነቶችና መልክዓ-ምድራዊ ሥፍራዎች በዘላቂነት እንዲቀጥሉና ተፈጥሯዊ ሚዛኗን ጠብቃ እንድትሄድ አበርክቶ እንዳለውም ገልፀዋል።

በተጨማሪም የሚተከሉ ችግኞች ለምግብ ዋስትና መረጋገጥና ለድህነት ቅነሳ ሥራዎች ያላቸው ሚና ወሳኝ ስለመሆኑ አንስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በተባበሩት መንግሥታት የምግብና የእርሻ ድርጅት የከበረውን የፋኦ አግሪኮላ ሜዳልያ ጥር 19 ቀን 2016 ዓ.ም በጣልያን ሮም በተካሄደ ሥነ-ሥርዓት መሸለማቸው ይታወሳል።

የእውቅና ሽልማቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የተበረከተላቸው በምግብ ዋስትና እና በተመጣጠነ የምግብ አቅርቦት ላሳዩት ርዕይ፣ የአመራር ቁርጠኝነት፣ ብሎም ፈጣን፣ ተለዋዋጭ እና ፈታኝ በሆኑ ከባቢዎች ስንዴን በማምረት በምግብ ራስን ለመቻል በተከተሉት ፈጠራዊ መፍትሔ ነው።

አሁን ላይ በኢትዮጵያ ከ6 ሺህ በላይ የእፅዋት ኃብቶች ያላት ሲሆን፤ ከነዚህም ውስጥ 600 ወይም 10 በመቶ የሚሆኑት በአገሪቱ ብቻ የሚገኙ ናቸው። 

ጎን ለጎንም የወፍ ዝርያዎችን ጨምሮ በየብስና በውኃ አካላት ውስጥ የሚኖሩ የተለያዩ ዓይነት ዝርያ ያላቸው በርካታ እንስሳት በኢትዮጵያ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ብዝኃ-ሕይወት ኢንስቲትዩት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ ባሉት ማዕከላት የተለያየ ጠቀሜታ ያላቸውን አገር በቀል እጽዋቶችን አዘጋጅቶ በማሠራጨት ላይ ይገኛል።

ኢንስቲትዩቱ አሁን ላይ በተለይም ለመጥፋት የተቃረቡ እጽዋቶችን በአገር በቀል ለመተካት ችግኞችን በስፋት  እያዘጋጀ መሆኑን ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም