ኢዜአ የኢትዮጵያን ስምና ተደማጭነት በዓለም መድረክ ከፍ ለማድረግ ያላትን እውነታ በተፈለገው ልክ ሊያሳይ ይገባል--ዶክተር ለገሰ ቱሉ - ኢዜአ አማርኛ
ኢዜአ የኢትዮጵያን ስምና ተደማጭነት በዓለም መድረክ ከፍ ለማድረግ ያላትን እውነታ በተፈለገው ልክ ሊያሳይ ይገባል--ዶክተር ለገሰ ቱሉ
አዲስ አበባ፤ጥር 21/2016(ኢዜአ)፦ኢዜአ የኢትዮጵያን ትክክለኛ ገፅታ በዓለም መድረክ ከፍ አድርጎ ለማሳየትና ተደማጭነቷን ለማጉላት ያላትን እውነታ በተፈለገው ልክ ተደራሽ ሊያደርግ እንደሚገባ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ ገለጹ።
አሰባሳቢ እና ታላቅ ትርክት በሆነው ህብረ ብሔራዊ አንድነት ላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
አንጋፋው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ያስገነባውን ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስ በዛሬው እለት የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት አስመርቋል።
በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ፤ ኢዜአ የኢትዮጵያን መልካም ገጽታና ከፍታ ለዓለም በማሳየት የላቀ አበርክቶ እንዳለው አውስተዋል።
ኢትዮጵያ ቀደምት ናት ስንል ቀደምት ተቋማትን በመገንባት መሆኑን ጠቅሰው፥ ለዚህም ኢዜአ ማሳያ እንደሆነ ተናግረዋል።
ኢዜአ ከሀገሪቱ ሁሉም ማዕዘናት እንዲሁም ከሌሎች ዓለማት ዜና እና ፕሮግራሞችን ለመገናኛ ብዙኃን በማድረስ እስካሁን የዘለቀ አንጋፋ ተቋም መሆኑን ገልፀዋል።
አዲስ ያስገነባው የሚዲያ ኮምፕሌክስም ዘመናዊ ቴክኖሎጂና መሠረተ-ልማቶችን ያሟላ በመሆኑ የኢትዮጵያን የሚዲያ አቅምና የመረጃ ተደራሽነት ከፍ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል።
በኢዜአ ውስጥ የተከናወኑ ሥራዎችም መንግስት የጀመራቸው የሚዲያ ሪፎርም ሥራዎች አንዱ አካል ነው ብለዋል።
ኢዜአ በኢትዮጵያ በሕብረ-ብሔራዊ አንድነትና የጋራ ትርክትን በመገንባት ሂደት የላቀ ድርሻውን በመወጣት ላይ እንደሚገኝም ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት።
ኢትዮጵያ የብዝኃነት አገር ናት ያሉት ዶክተር ለገሰ፥ አሰባሳቢ እና ታላቅ ትርክት በሆነው ህብረ ብሔራዊ አንድነት ላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ኢዜአ የኢትዮጵያን ስም በዓለም መድረክ ከፍ አድርጎ ለማስጠራት ያላትን እውነታ በአግባቡ አጉልቶ እንዲያሳይም አሳስበዋል።
ለተቋሙ ሥራዎች መሳካት የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍና እገዛ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ፤ ኢዜአ በአዲስ ምዕራፍ ብሔራዊ መግባባትና የሀገር ገፅታ ግንባታን ለማጠናከር ይሰራል ብለዋል።
ኢዜአ በሀገር ውስጥ ከሚገኙ የመገናኛ ብዙኃን በተጨማሪ ከውጭ ሀገራት ሚዲያዎች ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
በዚህም በአለም አቀፍ ደረጃ በሚዘጋጁ መድረኮች የኢትዮጵያን እውነቶች እንዲሁም ተጨባጭ የለውጥ ስራዎች አለም አቀፍ ሽፋን እንዲያገኙ እያደረገ መሆኑን አመላክተዋል።
በዛሬው እለት የተመረቀው የሚዲያ ኮምፕሌክስም መንግስት ለሚዲያው የሰጠውን ትኩረት የሚያሳይ መሆኑንም አንስተዋል።
ሀገራዊ ትርክትና ብሔራዊ መግባባትን ለማጠናከር የሥራ ቋንቋዎቹን ቁጥር እየጨመረ መሆኑን እና በቀጣናው ሀገራትም ቅርንጫፎችን ለመክፈት በዝግጅት ላይ መሆኑን ገልፀዋል።
የሚዲያ ኮምፕሌክሱ በቀጣይ ኢትዮጵያ ወደ ብልጽግና ለመሸጋገር በምታደርገው ጉዞ ውስጥ በአጀንዳ በመምራት፣ አገራዊ ነባራዊ ሀቆችን ዓለም እንዲያውቃቸው የሚከናወኑ ስራዎችን ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል።
ኢዜአ ያስመረቀው የሚዲያ ኮምፕሌክስ ዘመኑ የደረሰበትን የሚዲያ ቴክኖሎጂ ያሟላ ሲሆን፤ ሦስት የቴሌቪዥንና አራት የሬዲዮ ዘመናዊ ስቱዲዮችን አካቷል።
በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ ለሚዲያ ኮምፕሌክሱ ግንባታ መሳካት አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት እውቅና ተሰጥቷል።