ኮሚሽኑ ከአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራረመ - ኢዜአ አማርኛ
ኮሚሽኑ ከአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራረመ
አዲስ አበባ ፤ ጥር 21/2016 (ኢዜአ)፦የፌደራል ሥነ- ምግባርና ፀረ- ሙስና ኮሚሽን በመልካም ስነ- ምግባር የታነፀ የሰው ኃይል ለማፍራት የሚያስችለውን ስምምነት ከአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ጋር ተፈራረመ።
ስምምነቱን የፌደራል ሥነ-ምግባርና ፀረ- ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ እና የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ርዕሰ-አካዳሚ ዛዲግ አብርሃ ተፈራርመዋል።
የፌደራል ሥነ- ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ፤ ኮሚሽኑ ሙስና በሀገሪቱ ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ ለመከላከል የሚያስችሉ ሥራዎችን እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
የሙስና ትግሉን ለማጠናከር በመንግሥት ተቋማት፣ በልማት ድርጅቶችና በሌሎች ተቋማቶች ውስጥ የሚገኙ አመራሮችና ሠራተኞች በመልካም ስነ-ምግባር የታነፁ እና ብልሹ አሠራርን የሚታገሉ ሊሆኑ እንደሚገባ ገልፀዋል።
ይህንንም ለማድረግ በሥራ ላይ ለሚገኙ የሰው ኃይል የአቅም ግንባታ ሥልጠና የሚያገኙበትን ምቹ ሁኔታን መፍጠር በማስፈለጉ ዛሬ ከአካዳሚው ጋር ተፈራርመናል ብለዋል።
በቀጣይም ኮሚሽኑ በተቋማት ላይ የሚገኙ አመራሮችና ሠራተኞች ሙስናና ብልሹ አሠራር ያለውን የችግር ስፋት ተረድተው እራሳቸውን በመልካም ስነ-ምግባር እንዲያንፁ የሚያደርጉ ሥልጠናዎች በአካዳሚው የሚወስዱበት ዕድል ይፈጥራል ነው ያሉት።
የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ርዕሰ-አካዳሚ ዛዲግ አብርሃ በበኩላቸው፤ ስነ-ምግባርን መነሻ በማድረግ ሥራቸውን የማያከናውኑ ተቋማት እና አመራሮች ለሀገሪቱ ጥሩ ሥራን መሥራት አይችሉም ሲሉ ተናግረዋል።
በሀገሪቱ የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ የሚሰሩ ሥራዎች ስነ-ምግባርን ባከበረ መልኩ ሊሆን እንደሚገባ ገልፀዋል።
የዛሬ የስምምነት ፊርማ ከዘርፉ ጋር በተያያዘ የሰው ኃይልን የማሰልጠን ሥራዎች እንደሚከናወኑ ጠቁመዋል።
በተጨማሪም የተለያዩ አካላቶች የሚሳተፉበት ከመልካም ስነ-ምግባር ጋር የተያያዙ ውይይቶችና ክርክሮች የሚደረጉበት መድረክ እንደሚፈጠርም ጠቁመዋል።