ኢትዮ-ቴሌኮም /5ጂ/ ፈጣን የሞባይል ኔትወርክ አገልግሎት በሐረር ማስጀመሩ በተለይም ለተቋማት የጎላ ጠቀሜታ አለው

ሐረር፤ ጥር 21/2016(ኢዜአ)፦   ኢትዮ-ቴሌኮም  የአምስተኛው ትውልድ /5ጂ/ ፈጣን የሞባይል ኔትወርክ አገልግሎት በሐረርና ሃረማያ ማስጀመሩ በተለይም ለክልሉና ለአካባቢው  ተቋማት ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የታደሙ የተቋማቱ ተወካዮች ተናገሩ።

ኢትዮ - ቴሌኮም የአምስተኛው ትውልድ ፈጣንና የመጨረሻው  የሞባይል  ኔትዎርክ (5ጂ) አገልግሎት በሐረርና በሐረማያ ከተማና አካባቢው ትናንት አመሻሽ ላይ አስጀምሯል። 


 

በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የታደሙና አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የተቋማት ተወካዮች እንዳሉት ኢትዮ-ቴሌኮም የዓለማችንን ፈጣኑን ኔትዎርክ ማስጀመሩ የምንሰጠውን አገልግሎት ለማዘመን የጎላ ሚና አለው ።

የአዋሽ ባንክ የሐረር ቅርንጫፍ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ሱሌ አብዲ እንዳሉት፤ የአገልግሎቱ በክልሉ መጀመር በተለይም "የፋይናንስ ተቋማትን ሥራ በማዘመን ሕብረተሰቡን በበለጠ ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡

የ5ጂ ፈጣን የሞባይል ኔትወርክ  አገልግሎት መጀመሩ ዓለም ላይ ካሉ አጋሮቻቸውና ከተቋሙ ሃላፊዎች ጋር የሚያደርጉትን ውይይትና ሌሎች ስራዎች በተቀላጠፈ መልኩ እንዲያከናውኑ እንደሚያስችላቸው የተናገሩት ደግሞ በ'ኤስ ኦ ኤስ' የህጻናት መንደር በኢትዮጵያ የሐረር ፕሮግራም ዳይሬክተር አቶ አንዷለም ጌታቸው ናቸው።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀልን በቴክኖሎጂ በመታገዝ ለማከናወን ያቀደውን ስራ ስኬታማ ለማድረግ 5ጂ በክልሉ መጀመሩ አስፈላጊና ወቅቱን የጠበቀ ነው ያሉት ደግሞ የሐረሪ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ነስሪ ዘካርያ ናቸው።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የሐረሪ ክልል ከተማና ኮንስትራክሽን ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ አሚና አብዱልከሪም በበኩላቸው፤ የአገልግሎቱ መጀመር በከተማዋ ቀልጣፋ አሰራርን በማሳለጥ ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸው ገልጸዋል።

"የ5ጂ ፈጣን የሞባይል ኔትዎርክ አገልግሎት መጀመሩ በሁሉም ዘርፍ ለውጥ ያለው ስራ ለማከናወን  ያስችለናል" ብለዋል።

በሐረሪ ተገኝተው ፈጣኑን የሞባይል ኔትዎርክ(5ጂ) ያስጀመሩት የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬሕይወት ታምሩ በወቅቱ እንዳስታወቁት፤ አገልግሎቱ ለአካባቢው ማህበረሰብ በተለይም ለተቋማት የሚሰጠው ጠቀሜታ የጎላ ነው።


 

አገልግሎቱ "የሃገራችንን ኢኮኖሚ ማሳለጥ፣ ማህበራዊ እንቅስቃሴዎቻችንን ፈጣን በሆነ መልኩ መረጃን በመስጠትና በመቀበል ሂደት ትልቅ አቅም ያለው ማህበረሰብ ከመገንባት አኳያ የጎላ ፋይዳ እንዳለው ነው ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ ያመለከቱት።

ኢትዮ-ቴሌኮም እስካሁን ባደረጋቸው የአምስተኛው ትውልድ የሞባይል ኔትወርክ  አገልግሎት ማስፋፊያ ሥራዎች በምስራቁ የአገሪቱ ክፍል በጅግጅጋ፣ ድሬዳዋ፣ ሐረርና ሀረማያ ከተማና አካባቢውን  ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም