ቀጥታ፡

ኢዜአ የብሔር ብሔረሰቦች ድምፅነቱንና አሰባሳቢ ትርክት የመገንባት ሚናውን በአዲስ ምዕራፍ አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል- አፈ-ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር

አዲስ አበባ፣ ጥር 21/2016(ኢዜአ)፦ ኢዜአ የብሔር ብሔረሰቦች ድምፅነቱንና አሰባሳቢ ትርክት የመገንባት ሚናውን በአዲስ ምዕራፍ አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ።

ከተመሠረተ 82 ዓመታትን የተሻገረው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ያስገነባውን ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስ "ኢዜአ በአዲስ ምዕራፍ" በሚል መሪ ሀሳብ አስመርቋል።

በምርቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር፣ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉን ጨምሮ ሚኒስትሮች፣ የተቋማት አመራሮች፣ የሚዲያ ኃላፊዎችና ሌሎችም ተገኝተዋል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር፤ ኢዜአ ያስገነባው ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስ ምርቃት በይፋ አብስረዋል።

በዚሁ ጊዜ ባደረጉት ንግግርም ኢዜአ ረዥም እድሜ ያለውና የኢትዮጵያን ብሔር ብሔረሰቦች በማስተሳሰር እና ድምፅ በመሆን ረገድ ጉልህ አሻራ ያኖረ ተቋም ነው ብለዋል።

ኢዜአ ባለፈባቸው ዓመታት ሁሉ የኢትዮጵያውያን ድምፅ በመሆን ጉልህ ሚና መጫወቱን ያነሱት አፈ-ጉባዔው፤ በሀገሪቱ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ክስተቶችን በመዘገብ አይተኬ ታሪክ መጻፉን ተናግረዋል።

አፍሪካውያን በቅኝ ግዛት በነበሩበት ወቅት ለነፃነት በሚደረገው ትግል ድምፅ በመሆን ሲዘግብ የነበረ የፓን- አፍሪካኒዝም መሠረት መሆኑንም አውስተዋል።

ብዝኃ ማንነትን በእኩልነት በማስተናገድ ለሀገር አንድነት መጠናከር ወሳኝ በመሆኑ፤ መገናኛ ብዙኃን አስተሳሳሪ ትርክት ላይ በትኩረት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አንድነትንና መተባበርን የሚያጠናክር ብሔራዊ መግባባትን የመፍጠርና የሀገር ገፅታ ግንባታ ተልዕኮውን በአግባቡ እየተወጣ ስለመሆኑም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስጠብቁ መረጃዎችን በተለያዩ የውጭ ቋንቋዎች ተደራሽ በማድረግም ግንባር ቀደም መሆኑን ገልፀዋል።

አዲስ ያስገነባው ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስም አገልግሎቱን ለላቀ ሀገራዊ ተልዕኮ ዝግጁ የሚያደርግ፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች የተሟሉለትና ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ነው ብለዋል።

ኢዜአ ወቅታዊና አንገብጋቢ የሀገርና የሕዝብ አጀንዳዎችን በላቀ ሁኔታ ተደራሽ ለማድረግ የኢትዮጵያን ትክክለኛ ገፅታ ለመገንባት አሁን ካለው የላቀ ሥራ እንደሚጠብቀውም ገልፀዋል።

በመላው ሀገሪቱ በከፈታቸው ቅርንጫፎቹ የብሔር ብሔረሰቦች ድምፅ በመሆን አሰባሳቢ ትርክት የመገንባት ሚናውን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።

ከውጭ ሀገራት ዜና አገልግሎቶች ጋር እያደረገ ያለውን ትስስር በማጠናከር፣ ከአፍሪካ በአስተማማኝ የዜና ምንጭነቱ ቀዳሚ ለመሆን የያዘውን ራዕይ ለማሳካት እንዲተጋም አሳስበዋል።

የኢዜአ የሚዲያ ኮምፕሌክስ ዘመኑ የደረሰበትን የሚዲያ ቴክኖሎጂ ያሟላ ሲሆን፤ ሦስት የቴሌቪዥንና አራት የሬዲዮ ዘመናዊ ስቱዲዮችን አካቷል። 

በተጨማሪም ለቢሮ አገልግሎት የሚሆኑ በርካታ ክፍሎች፣ የመሰብሰቢያ አዳራሾች፣ ቤተ-መጽሐፍት፣ የመዝናኛ ማዕከልና ዘመናዊ ጂምናዝየም አሉት።

አንጋፋው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት(ኢዜአ) ብሔራዊ መግባባት የመፍጠርና የሀገር ገፅታ ግንባታ ተልዕኮውን ለማሳካት ዜና እና ዜና ነክ መረጃዎችን ተደራሽ በማድረግ ላይ ይገኛል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም