ቀጥታ፡

ኢዜአ በአዲስ ምዕራፍ የኢትዮጵያን ገጽታ ለዓለም ለማሳወቅና ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር ይሰራል

አዲስ አበባ፣ ጥር 21/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በአዲስ ምዕራፍ የኢትዮጵያን ገጽታ ለዓለም ለማሳወቅና ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር እንደሚሰራ የኢዜአ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ ገለጹ።

አንጋፋው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ያስገነባውን ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስ "ኢዜአ በአዲስ ምዕራፍ" በሚል መሪ ሀሳብ አስመርቋል።


 

በዚሁ ወቅት ንግግር ያደረጉት የኢዜአ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ፤ ኢዜአ በአዲስ ምዕራፍ ብሔራዊ መግባባትና የሀገር ገፅታ ግንባታን ለማጠናከር ይሰራል ብለዋል።

ኢዜአ በውጭ ከሚገኙ የዜና አገልግሎቶች እኩል የሚሆን ተወዳዳሪነት ያለው ተቋም ነው ብለዋል።

ኢዜአ በሀገር ውስጥ ከሚገኙ የመገናኛ ብዙኃን በተጨማሪ ከውጭ ሀገራት ሚዲያዎች ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

ኢዜአ ላለፉት 82 ዓመታት የሀገርን ገፅታና እውነታን ለዓለም ተደራሽ በማድረግ ላይ የሚገኝ መሆኑን ጠቁመዋል።

 የኢትዮጵያን የለውጥ ጉዞ ትርጉም ባለው መልኩ ለሕዝብ ተደራሽ ለማድረግና ለዓለም ለማሳወቅም ይተጋል ነው ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው። 

ኢዜአ ዓለም አቀፋዊ አድማሱን እያሰፋ እንደሆነ ጠቅሰው፤  የብሪክስ የሚዲያ ሥራ አስፈጻሚ አባል እንዲሆን መጋበዙንም ጠቅሰዋል።

የኢዜአ የሚዲያ ኮምፕሌክስ መንግሥት የያዘው የሚዲያ ተቋማት ግንባታ የሪፎርም ማሳያ መሆኑን ገልፀዋል። 

ኢዜአ በአዲስ ምዕራፍ ሀገራዊና አህጉራዊ ተቋም በመሆን የኢትዮጵያን ገፅታ በላቀ ደረጃ ለመገንባት እንደሚሰራ ተናግረዋል። 

ሀገራዊ ትርክትና ብሔራዊ መግባባትን ለማጠናከር የሥራ ቋንቋዎቹን ቁጥር እየጨመረ ሲሆን፤ በቀጣናው አገራትም ቅርንጫፎችን ለመክፈት በዝግጅት ላይ መሆኑን ገልፀዋል። 

ኢትዮጵያ ድንበር ተሻጋሪ ሚዲያ እንዲኖራት ኢዜአ ፈር ቀዳጅ ሆኖ ይሰራል ብለዋል። 

ለዚህም አዲስ ያስገነባውን የሚዲያ ኮምፕሌክስ በአግባቡ ለመጠቀም ይተጋል ነው ያሉት።

የኢዜአ የሚዲያ ኮምፕሌክስ ዘመኑ የደረሰበትን የሚዲያ ቴክኖሎጂ ያሟላ ሲሆን፤ ሦስት የቴሌቪዥንና አራት የሬዲዮ ዘመናዊ ስቱዲዮችን አካቷል። 

በተጨማሪም ለቢሮ አገልግሎት የሚሆኑ በርካታ ክፍሎች፣ የመሰብሰቢያ አዳራሾች፣ ቤተ-መጽሐፍት፣ የመዝናኛ ማዕከልና ዘመናዊ ጂምናዚየም አሉት።

ከተመሠረተ 82  ዓመታት የሆነው አንጋፋው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ብሔራዊ መግባባት የመፍጠርና የሀገር ገፅታ ግንባታ ተልዕኮውን ለማሳካት ዜና እና ዜና ነክ መረጃዎችን ተደራሽ በማድረግ ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም