የኢዜአ ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስ የኢትዮጵያን የሚዲያ አቅምና ተደራሽነት ከፍ የሚያደርግ ነው- ዶክተር ለገሰ ቱሉ - ኢዜአ አማርኛ
የኢዜአ ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስ የኢትዮጵያን የሚዲያ አቅምና ተደራሽነት ከፍ የሚያደርግ ነው- ዶክተር ለገሰ ቱሉ
አዲስ አበባ፣ ጥር 21/2016(ኢዜአ)፦ የኢዜአ ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስ የኢትዮጵያን የሚዲያ አቅምና ተደራሽነት ከፍ የሚያደርግ መሆኑን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ ገለጹ።
በኢትዮጵያ በሕብረ-ብሔራዊ አንድነትና የጋራ ትርክትን በመገንባት ሂደት ኢዜአ የላቀ ድርሻውን በመወጣት ላይ መሆኑንም ተናግረዋል።
አንጋፋው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ያስገነባውን ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስ በዛሬው እለት አስመርቋል።
በምርቃት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ፤ ኢዜአ የኢትዮጵያን መልካም ገጽታና ከፍታ ለዓለም በማሳየት የላቀ አበርክቶ እንዳለው ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ ቀደምት ናት ስንል ቀደምት ተቋማትን በመገንባት ነው ብለዋል።
ኢዜአ ከሀገሪቷ ሁሉም ማዕዘናት እንዲሁም ከሌሎች ዓለማት ዜና እና ፕሮግራሞችን ለመገናኛ ብዙኃን በማድረስ እስካሁንም የዘለቀ አንጋፋ ተቋም መሆኑን ገልፀዋል።
አዲስ ያስገነባው የሚዲያ ኮምፕሌክስም ዘመናዊ ቴክኖሎጂና መሠረተ-ልማቶችን ያሟላ በመሆኑ የኢትዮጵያን የሚዲያ አቅምና የመረጃ ተደራሽነት ከፍ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል።
በኢዜአ ውስጥ የተከናወኑ ሥራዎችም የሚዲያ ሪፎርም ሥራዎች አንዱ አካል መሆኑንም ጠቁመዋል።
ኢዜአ በኢትዮጵያ በሕብረ-ብሔራዊ አንድነትና የጋራ ትርክትን በመገንባት ሂደት የላቀ ድርሻውን በመወጣት ላይ መሆኑንም ተናግረዋል።
በመሆኑም ለተቋሙ ሥራዎች መሳካት የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍና እገዛ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
የኢዜአ የሚዲያ ኮምፕሌክስ ዘመኑ የደረሰበትን የሚዲያ ቴክኖሎጂ ያሟላ ሲሆን፤ ሦስት የቴሌቪዥንና አራት የሬዲዮ ዘመናዊ ስቱዲዮችን በውስጡ አካቷል።
ከተመሠረተ 82 ዓመታትን የተሻገረው አንጋፋው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ብሔራዊ መግባባት የመፍጠርና የሀገር ገፅታ ግንባታ ተልዕኮውን ለማሳካት ዜና እና ዜና ነክ መረጃዎችን ተደራሽ በማድረግ ላይ ይገኛል።