ኢዜአ የአገር ባለውለታ አንጋፋ ተቋም ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
ኢዜአ የአገር ባለውለታ አንጋፋ ተቋም ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ ጥር 21/2016 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የአገር ባለውለታ አንጋፋ ተቋም መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
አንጋፋው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት /ኢዜአ/ ያስገነባውን ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስ አስመርቋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኢዜአ ዘመኑን በሚዋጅ ቴክኖሎጂ ተደራጅቷል።
ኢዜአ ባለፉት በርካታ ዓመታት ዜናዎችን፣ መረጃዎችን ከአገር ውስጥ እና ከመላው ዓለም ለህዝብ ተደራሽ ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸዋል።
በአሁኑ ጊዜም ዘመኑን የሚዋጁ ቴክኖሎጂዎችን ማሟላቱን መመልከታቸውን ጠቁመው፤ የኢትዮጵያን እውነታ ለመላው ዓለም ማሳወቅ አስተማማኝ ደረጃ ላይ መሆኑን አያይዘው ገልጸዋል።
ኢዜአ ከዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ጎን ለጎን በሰው ሃይል እና በሌሎችም ቁሳቁስ ተደራጅቶ መመልከታቸውንም አክለዋል።
የኢትዮጵያን እውነታ ከፍ ማድረግ የሚችሉ ስራዎችን በመስራት በዓለም አደባባይ የኢትዮጵያን እውነታ ለማሳወቅ ይበልጥ መስራት እንዳለበትም ጠቁመዋል።
የኢዜአ ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስ ለአካባቢው ተጨማሪ ውበት መፍጠር መቻሉን ገልጸዋል።
የከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን ጠቁመዋል።
የኢዜአ የሚዲያ ኮምፕሌክሱ ዘመኑ የደረሰበትን የሚዲያ ቴክኖሎጂ ያሟላ ሲሆን ሦስት የቴሌቪዥንና አራት የሬዲዮ ዘመናዊ ስቱዲዮዎችን አካቷል።
በተጨማሪም ለቢሮ አገልግሎት የሚሆኑ በርካታ ክፍሎች፣ የመሰብሰቢያ አዳራሾች፣ ቤተ-መጽሀፍት፣ የመዝናኛ ማዕከልና ዘመናዊ ጂምናዝየም አሉት።
ከተመሠረተ 82 ዓመታት የሆነው አንጋፋው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ብሔራዊ መግባባት የመፍጠርና የሀገር ገፅታ ግንባታ ተልዕኮውን ለማሳካት ዜና እና ዜና ነክ መረጃዎችን ተደራሽ በማድረግ ላይ ይገኛል።
ተቋሙ ያስገነባው ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስም በዛሬው እለት በደማቅ ሥነ ስርዓት እየተመረቀ ነው።
በምርቃት ሥነ-ስርዓቱ ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉን ጨምሮ ሌሎችም ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የሚዲያ አመራሮችና ሌሎችም እንግዶች ተገኝተዋል።