የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ያስገነባውን ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስ ዛሬ ያስመርቃል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ያስገነባውን ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስ ዛሬ ያስመርቃል
አዲስ አበባ፣ ጥር 21/2016(ኢዜአ)፦ አንጋፋው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት(ኢዜአ) ያስገነባውን ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስ በዛሬው እለት ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት ያስመርቃል።
የሚዲያ ኮምፕሌክሱ ዘመኑ የደረሰበትን የሚዲያ ቴክኖሎጂ ያሟላ ሲሆን ሦስት የቴሌቪዥንና አራት የሬዲዮ ዘመናዊ ስቱዲዮዎችን አካቷል።
በተጨማሪም ለቢሮ አገልግሎት የሚሆኑ በርካታ ክፍሎች፣ የመሰብሰቢያ አዳራሾች ቤተ-መጽሀፍት፣ የመዝናኛ ማዕከልና ዘመናዊ ጂምናዝየምም አሉት።
ከተመሠረተ 80 ዓመታትን የተሻገረው አንጋፋው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት(ኢዜአ) ብሔራዊ መግባባት የመፍጠርና የሀገር ገፅታ ግንባታ ተልዕኮውን ለማሳካት ዜና እና ዜና ነክ መረጃዎችን ተደራሽ በማድረግ ላይ ይገኛል።
ለዚህም በመላው ሀገሪቱ 38 ቅርንጫፎችን በመክፈት በቅርቡ የጀመራቸውን ሶማሊኛ እና አፋርኛን ጨምሮ በአማርኛ፣ በአፋን ኦሮሞና በትግርኛ ቋንቋዎች አስተማማኝ የዜና ምንጭ ሆኖ ቀጥሏል።
በእንግሊዝኛ፣ በአረብኛ እና በፈረንሳይኛ ቋንቋዎችም የኢትዮጵያን ገፅታና እውነታ ለዓለም ተደራሽ እያደረገ ይገኛል።
ኢዜአ በ2022 በአፍሪካ ተምሳሌት፣ አስተማማኝና ተጽዕኖ ፈጣሪ የዜና ምንጭ የመሆን ራዕዩን ለማሳካት በላቀ ብቃት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።
የስርጭትና ተደራሽነት አድማሱን በምስራቅ አፍሪካ ለማስፋትም በኬንያና በጅቡቲ ቅርንጫፎችን ለመክፈት በዝግጅት ላይ ነው።
ኢዜአ በ1934 ዓ.ም በወቅቱ የጽሕፈት ሚኒስቴር ተብሎ ይጠራ በነበረው ተቋም፣ የጋዜጣ እና ማስታወቂያ ጽህፈት ቤት ስር እንደ አንድ የሥራ ክፍል መቋቋሙ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት(ኢዜአ) የሚለውን መጠሪያና የዜና አገልግሎት ደረጃ ያገኘው በ1960 ዓ.ም በወጣው የመጀመሪያው የማቋቋሚያ አዋጅ ነው።
በአዋጅ ቁጥር 1115/2011 በሀገር ውስጥና በውጪ ሀገር ዋነኛ የዜና ምንጭ በመሆን ብሔራዊ መግባባትን የመፍጠርና የሀገሪቱን ገጽታ የመገንባት ተልዕኮ ተሰጥቶታል።
ኢዜአ እስከ አሁን በመጣበት ረጅም የአገልግሎት ዘመን በሀገሪቱ በተመዘገቡ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ስኬቶች ላይ የራሱን አሻራ እያሳረፈ ጉዞውን ቀጥሏል።
አገልግሎቱ በአዲስ የከፍታ ምዕራፍ በኢትዮጵያና በህዝቦቿ ጥቅም ላይ ያተኮሩ ዜና እና ዜና ነክ ዘገባዎችንና ፕሮግራሞችን በፍጥነትና በጥራት ለህዝብ ተደራሽ የሚያደርግ ይሆናል።