የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የአየር ንብረት ለውጥን ከመከላከል ባለፈ የምግብ ዋስትና መሰረት ሆኗል- ግብርና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የአየር ንብረት ለውጥን ከመከላከል ባለፈ የምግብ ዋስትና መሰረት ሆኗል- ግብርና ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤ ጥር 20/2016(ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የአየር ንብረት ለውጥን ከመከላከል ባለፈ የምግብ ዋስትና መሰረት መሆኑን የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር እያሱ ኤልያስ ገለፁ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት የተጀመረውና አምስት ዓመታትን ያስቆጠረው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ቱርፋቶች በተግባር እየታዩ መጥተዋል።
ከ2011 ዓ.ም እስከ 2015 ዓ.ም የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ32 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸው ይታወቃል።
በዚህም የተፈጥሮ ሃብትን በመጠበቅ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የሚኖረው አስተዋጽኦ እንዳለ ሆኖ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ሁነኛ አማራጭ ሆኗል።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር እያሱ ኤሊያስ፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብሩ ዓለምን ስጋት ላይ ለጣለው የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የአየር ንብረት ለውጥን ከመከላከል ባለፈ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራና ሌሎችም ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም በአትክልትና ፍራፍሬ ተክሎች ወይም የጥምር ደን ልማት ስራዎች ዜጎች የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ ከማስቻል ባለፈ ምርታቸውን ወደ ገበያ በማውጣት ተጨማሪ ገቢ እንዲያመነጭ ያስችላል ነው ያሉት።
ከሚተከሉት ችግኞች ከ60 በመቶው በአርሶ አደሩ ማሳ ላይ መሆናቸውን ጠቅሰው ይህም ለምግብ ዋስትና እና የገቢ ምንጭ ትልቅ አቅም እየፈጠረ መምጣቱን አንስተዋል።
በአረንጓዴ አሻራ የለማ አቦካዶ ለምርት ደርሶ ወደ ውጭ ገበያ ማቅረብ የተቻለበትንም ውጤታማ ስራ አንስተዋል።
በሌላ በኩል በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የለማው የመኖ ልማት አርሶ እና አርብቶ አደሩ ማህበረሰብ ለእንስሳቱ በቂ መኖ እንዲያገኝ በማስቻል የእንሰሳት ተዋጽኦ ምርታማነት ማሳደጉን ተናግረዋል።
የእንስሳት ተዋጽኦ ምርታማነት መጨመር ደግሞ በተመጣጠነ ምግብ ዕጦት ሳቢያ በሕጻናት ዕድገት ላይ ሲስተዋል የነበረውን ችግር እያቃለለ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ከዚህ ጋር የተያያዘ ከአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በኋላ የተጀመረው የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብርም በዜጎች የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት ላይ ተጨማሪ አቅም መፍጠሩን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት የከበረውን የፋኦ አግሪኮላ ሜዳልያ ትላንት መሸለማቸው ይታወሳል።
የዕውቅና ሽልማቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የተበረከተላቸው በምግብ ዋስትና እና በተመጣጠነ የምግብ አቅርቦት ላሳዩት ርዕይ፣ የአመራር ቁርጠኝነት፣ ብሎም ፈጣን፣ ተለዋዋጭ እና ፈታኝ በሆኑ ከባቢዎች ስንዴን በማምረት በምግብ ራስን ለመቻል በተከተሉት ፈጠራዊ መፍትሔ ነው፡፡