የባለቤትነት መብት ህግ መሻሻል የፈጠራ ስራዎችን በበቂ ሁኔታ ተደራሽ ለማድረግ ጉልህ አስተዋጽኦ አለው - ኢዜአ አማርኛ
የባለቤትነት መብት ህግ መሻሻል የፈጠራ ስራዎችን በበቂ ሁኔታ ተደራሽ ለማድረግ ጉልህ አስተዋጽኦ አለው
አዲስ አበባ፤ ጥር 20/2016(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ ለፈጠራ ስራዎች የተሰጠው ትኩረት የታለመለትን አላማ እንዲያሳካ እየተሻሻለ ያለው የባለቤትነት መብት ህግ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለስልጣን አስታወቀ።
በኢትዮጵያ ላለፉት 30 ዓመታት በስራ ላይ የነበረውንና እየተሻሻለ ያለውን የባለቤትነት መብት ህግ አስመልክቶ ለባለድርሻ አካላት ገለፃ ተደርጓል።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ወልዱ ይመስል በዚሁ ጊዜ በኢትዮጵያ ቴክኖሎጂያዊ አሰራሮችን ተግባራዊ በማድረግ ረገድ መልካም ጅምሮች እንዳሉ አንስተዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ጥቅም ላይ እየዋሉ ከሚገኙ የቴክኖሎጂ ውጤቶች በተጨማሪ በፈጠራ የሚበለፅጉ ቴክኖሎጂዎች ለሀገር ዕድገት የጎላ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ ብለዋል።
በኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ ፈጠራ ዙሪያ ያለው ተሞክሮ እምብዛም በመሆኑ አገር በቀል ቴክኖሎጂዎችን በመፍጠር ለዓለም አቀፍ ገበያ ለማቅረብ ብዙ መስራት ይጠይቃል።
በዚህ ረገድ በኢትዮጵያ በአእምሯዊ ንብረትነት የተመዘገቡ ውጤቶች 658 ብቻ መሆናቸውን ጠቅሰው ዘመኑ የሚጠይቀውን ቴክኖሎጂ ያሟሉ የፈጠራ ስራዎች በስፋት የሚወጡበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠር አስፈላጊ ነው ብለዋል።
ለዚህም የፓተንት ህጉን በማሻሻል የፈጠራ ስራዎች በስፋት የሚወጡበትንና ሙያተኞች የሚበቁበትን ዕድል መፍጠር አንዱና ዋነኛው ተልዕኮ መሆኑን አስረድተዋል።
ይህን ተከትሎ ላለፉት 30 ዓመታት በስራ ላይ የነበረውን የፓተንት ህግ የማሻሻል ስራዎች መጀመራቸውን ተናግረዋል ።
ህጉ አሁናዊ አለም አቀፍ ተሞክሮዎችንና ልምዶችን ያካተተና በዘርፉ የተሻለ ልምድ ያላቸውን አካላት ሃሳብ ያቀፈ መሆኑን ገልጸዋል።
የፍትህ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኤርሚያስ የማነብርሃን የኢትዮጵያ የባለቤትነት መብት ስርዓት በሚል ርእስ እየተሻሻለ ያለውን ህግ አስመልክተው ገለጻ አድርገዋል።
በኢትዮጵያ ያለው ህግ ከ30 ዓመት በላይ የቆየ በመሆኑ ዓለም አቀፍ ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን ከግምት ለማስገባት አዳጋች አድርጎታል።
በመሆኑም የባለቤትነት መብት ህግን በማሻሻል የፈጠራ ውጤቶች ለወሳኝ የልማት ስራዎች ግብዓት እንዲሆኑ መስራት አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።
እየተሻሻለ ያለው ህግ ''መፍጠርና መፍጠን'' የሚለውን ጽንሰ ሃሳብ ተግባር ላይ በማዋል ረገድ ያሉ ክፍተቶችን ይሞላል ተብሎ ታምኖበታል።
በዋናነት የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ የሚያቃልሉና ሀገሪቱ እያከናወነች ላለው ልማት አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ሀገር በቀል የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በስፋት ለማምረት ያስችላል ብለዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር አማካሪ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፎዚያ አሚን በበኩላቸው ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የፈጠራ ስራዎች የማይተካ ሚና አላቸው።
እየተሻሻለ ያለው የባለቤትነት መብት ህግ መንግስት በዘርፉ እያከናወነ ያለውን ጥረት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያደርሱና ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያላቸው የፈጠራ ውጤቶች እንዲወጡ ያስችላል ብለዋል።
በተጨማሪም የፈጠራ ባለቤቶች እና ሀገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት ያለባቸውን ጥቅም በተገቢው መንገድ እንዲያገኙ የሚደግፍ በመሆኑ የህጉ መሻሻል አስፈላጊ ነው ብለዋል።