የኢትዮጵያን የትብብርና በጋራ የመልማት እቅድ ሀገራት ሊደግፉት ይገባል - አምባሳደሮች - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን የትብብርና በጋራ የመልማት እቅድ ሀገራት ሊደግፉት ይገባል - አምባሳደሮች
አዲስ አበባ፤ ጥር 20/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያን የሰጥቶ መቀበል የትብብርና በጋራ የመልማት እቅድ ሀገራት ሊደግፉት እንደሚገባ በአሜሪካ፣ ቻይና እና ካናዳ የኢትዮጵያ አምባሳደሮች ገለጹ።
ታህሳስ 22 ቀን 2016 ዓ.ም ኢትዮጵያ የባህር በር የምታገኝበትን የመግባቢያ ስምምነት ከሶማሊ ላንድ ጋር መፈራረሟ ይታወሳል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው በአሜሪካ፣ ቻይና እና ካናዳ የኢትዮጵያ አምባሳደሮች የባህር በር ስምምነቱ በሰጥቶ መቀበል መርህ በጋራ የመልማት ዓላማን የሰነቀ መሆኑን ገልጸዋል።
በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ፤ የኢትዮጵያ የባህር በር ፍላጎትና የወደብ ጥያቄ የህልውና ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።
ከ120 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ባላት ሀገር፣ ሰፊ የልማትና የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገበች ላለች ሀገር የባህር በር በእጅጉ ያስፈልጋታል ብለዋል።
በቀይ ባህር አካባቢና አጠቃላይ በቀጣናው የሰላምና ጸጥታ ጉዳይ ኢትዮጵያ የመሪነት ሚናዋን ለመወጣትም እንዲሁ።
በመሆኑም የኢትዮጵያ እና ሶማሊ ላንድ የባህር በር ስምምነት ከሀገራዊ የጋራ ጥቅም ባለፈ አህጉራዊ ፋይዳ ያለው መሆኑን አምባሳደር ስለሺ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ከሱማሊ ላንድ ጋር ያደረገችው ስምምነት በሰጥቶ መቀበልና በጋራ የመልማት መርህን በተከተለ መልኩ መሆኑንም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ አካሄድ ለጎረቤት ሀገራት ቅድሚያ የሚሰጥ፤ በጋራ የመልማትና የጋራ ተጠቃሚነትን መርህ ያደረገ እንዲሁም የሀገርን ክብርና ጥቅም የሚያስከብር መሆኑንም አስረድተዋል።
በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈራ ደርበው፤ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ በጋራ የመልማት አላማን የሰነቀ በመሆኑ ሁሉም በዚሁ መልኩ ሊገነዘበው ይገባል ብለዋል።
በመሆኑም የኢትዮጵያን የትብብርና በጋራ የመልማት አላማ የቀጣናውም ይሁን የአለም ሀገራት ሊደግፉት ይገባል ነው ያሉት።
በካናዳ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍጹም አረጋ፤ የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ መርህ የልማት ትስስርን በማጠናከር የጋራ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም ከጎረቤት ሀገራት ጋር በትራንስፖርትና የቴሌኮም መሰረተ ልማት ጠንካራ ትስስር እንዲፈጠር እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
በኤሌክትሪክና የውሃ አቅርቦትም ጎረቤት ሀገራት እንዲጠቀሙ ኢትዮጵያ በቁርጠኝነት እየሰራች መሆኑን ገልጸው የባህር በር ስምምነቱም ተመሳሳይ አላማ የሰነቀ መሆኑን ገልጸዋል።
በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር፤ የባህር በር ስምምነቱ የአብሮ መልማት፣ ማደግና የትብብር መርህን የተከተለ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላምና ደህንነት ላይ ያላትን የላቀ ሚና በብቃት ለመወጣት እንዲሁም አህጉራዊ ልማትን ለማፋጠን የባህር በር ስምምነቱ የተሻለ እድል ይዞ እንደሚመጣ ይታመናል ብለዋል።