የሺልድቫክስ ኢንተርፕራይዝ ፕሮጀክት ግንባታ በይፋ ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የሺልድቫክስ ኢንተርፕራይዝ ፕሮጀክት ግንባታ በይፋ ተጀመረ
አዲስ አበባ፤ ጥር 20/2016(ኢዜአ)፦ የሺልድቫክስ ኢንተርፕራይዝ ፕሮጀክት ግንባታ በይፋ ተጀመረ
የሺልድቫክስ ኢንተርፕራይዝ ፕሮጀክት በአገር ውስጥ ክትባቶችን በማምረት በቀጣናው ትልቅ ለውጥ ማምጣት የሚችልና ተስፋ የተጣለበት መሆኑ ተጠቁሟል።
ግንባታው በቂሊንጦ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ውስጥ የሚከናወን ሲሆን የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ የግንባታ ማስጀመሪያ የመሰረተ ድንጋይ አስቀምጠዋል።
ዶክተር ሊያ ታደሰ በዚሁ ወቅት የሺልድቫክስ ኢንተርፕራይዝ ፕሮጀክት ጠንካራ የጤና ስርአት ለመገንባት ታስቦ ነሐሴ 24 ቀን 2014 በሚኒስትሮች ምክር ቤት መቋቋሙን ገልጸዋል።
ይህ የመንግስት የልማት ድርጅት ኢትዮጵያ በክትባት ማምረት ዘርፍ የነበራትን ነባር እውቀቶች በማዋሃድ በአዲስ መልክ ወደ ስራ የሚገባ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም የኢትዮጵያን የጤና ስርዓት ከማሻሻል ባለፈ ለቀጣናው ትልቅ ተስፋ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የሺልድቫክስ ኢንተርፕራይዝ ፕሮጀክት በ2027 የክትባት ንጥረ-ነገሮችን የማምረት ተግባር እንዲጀምር ዕቅድ መያዙን ገልጸዋል።
በዚህም የፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ተቋቁሞ ወደ ስራ መገባቱን ጠቁመዋል።
የሺልድቫክስ ኢንተርፕራይዝ ፕሮጀክት የቀጣናውን የጤና ስርዓት ለማሻሻል ወሳኝ ሚና የሚጫወት መሆኑንም ተናግረዋል።
ለፕሮጀክቱ እውን መሆን ድጋፍ ያደረጉትን የዓለም ባንክ፣ የዓለም ጤና ድርጅት፣ ሲዲሲ-አፍሪካን እና ሌሎች ተቋማትን አመስግነዋል።
በኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ሱዳን እና ደቡብ ሱዳን የዓለም ባንክ ዳይሬክተር ኦስማን ዲዮን፤ ባንኩ በኢትዮጵያ ጠንካራ የጤና ስርዓት እንዲኖር የበኩሉን ሃላፊነት እየተወጣ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
የሺልድቫክስ ኢንተርፕራይዝ ፕሮጀክት ውጤታማ እንዲሆን አስፈላጊውን እገዛ እንደሚደርጉ ጠቁመዋል፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አክሊሉ ታደሰ በበኩላቸው ኢንተርፕራይዙ መንግስት ለአገር ውስጥ አምራቾች እና ባለሃብቶች ለሰጠው ልዩ ትኩረት ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ በዓለም ጤና ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ፣ የሲዲሲ-አፍሪካ ተወካይ እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።