ቀጥታ፡

የአየር ንብረት ለውጥና ህገ ወጥ ንግድ በዓለም ላይ ለዱር እንስሳት ቁጥር መመናመን ዋነኛ ምክንያት ሆኗል

አዲስ አበባ፤ ጥር 20/2016(ኢዜአ)፦የአየር ንብረት ለውጥና ህገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ በዓለም ላይ ለዱር እንስሳት ቁጥር መመናመን ዋነኛ ምክንያት መሆኑ ተገለጸ።

በዓለም ላይ የአቦሸማኔን የመጥፋት አደጋ ለመከላከል ዓላማ ያደረገ ጉባዔ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

የአቦሸማኔ ጥበቃ ፈንድ በዓለም ላይ ለአቦሸማኔዎች ጥበቃ ለማድረግ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1990 በናሚቢያ ዋና ከተማ ዊንድሆክ የተመሠረተ ዓለም አቀፍ ድርጅት ነው።

በዓለም ላይ የአቦሸማኔዎች ቁጥር ባለፉት 100 ዓመታት 90 በመቶ በመቀነስ በእጅጉ እያሽቆለቆለ መጥቶ ከ100 ሚሊየን አሁን ላይ 10 ሚሊየን መድረሱን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

በመሆኑም የአቦሸማኔ ጥበቃ ፈንድ ከተመሠረተ ጀምሮ እስካሁን አገራትን በማስተባበር በዓለም ላይ ለአቦሸማኔዎች ጥበቃ በማድረግ ላይ ይገኛል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ በአዲስ አበባ የሚመክረውን ጉባዔም የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ከዓለም አቀፍ የአቦሸማኔ ጥበቃ ፈንድ (ቺታ ኮንሰርቬሽን ፈንድ) ጋር በመተባበር ያዘጋጁ መሆኑም ታውቋል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ፤ በኢትዮጵያ ፖርኮችን በመገንባትና የተፈጥሮ ኃብቶችን በመጠበቅ ለዱር እንስሳት ጥበቃ በመደረግ ላይ መሆኑን ገልፀዋል።

ለዱር እንስሳት መጥፋትና መሰደድ በተለይም የአየር ንብረት ለውጥ፣ የደን ምንጣሮ፣ ሕገ-ወጥ የዱር እንስሳት ንግድና ሌሎችም ዓይነተኛ ምክንያቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ ከሚገኙ በርካታ የዱር እንስሳት መካከል አቦሸማኔም መኖሩን የጠቀሱት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በተለያዩ ችግሮች እንዳይጠፉ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ለኅብረተሰቡ በጉዳዩ ላይ ግንዛቤ የመፍጠርና ሁሉንም ያሳተፈ ጥበቃ ማድረግ እንዲሁም የአረንጓዴ አሻራ ልማትና የፓርኮች ጥበቃ ሥራ ይጠቀሳሉ ብለዋል። 


 

የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን  ዋና ዳይሬክተር ኩመራ ዋቅጅራ፤ የፓርኮችን ልማት ከዱር እንስሳት ጥበቃ ባለፈ ለተፈጥሮ ኃብት ጥበቃና ለቱሪዝም ኃብት እንዲያገለግሉ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ የዱር እንስሳትን ከጥፋት ለመታደግ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸው፤ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡ 


 

የዓለም አቀፍ የአቦሸማኔ ፈንድ መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፕሮፌሰር ላውሪ ማርከር፤ የጉባዔው ዓላማ በዱር እንስሳትና ውጤቶቻቸው ላይ የሚታየውን ሕገ-ወጥ ንግድና አደን ለመከላከል የሚያስችል ትብብር ለመፍጠር ነው ብለዋል።

በተለይም አቦሸማኔ በዓለም ላይ ቁጥሩ እያሽቆለቆለ የመጥፋት አደጋ የተጋረጠበት መሆኑን ጠቅሰው፤ በጋራ የመጠበቅ አደራ አለብን ብለዋል።

አሁን ላይ በ23 የአፍሪካ አገራት 7 ሺህ 500 አቦሸማኔዎች እንዳሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም