የአማራ ክልል አመራር አባላት የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት አካል የሆነውን የሎጎ ሃይቅ ጎበኙ

ደሴ ፤ ጥር 20/2016 (ኢዜአ)፡- የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዱ ሁሴን እና ሌሎች የክልልና የደቡብ ወሎ ዞን አመራር አባላት በገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት መርሀግብር የሚለማውን የሎጎ ሐይቅ  ጎብኙ።

የደቡብ ወሎ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን መምሪያ ሃላፊ አቶ እያሱ ዮሐንስ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት፤ በዞኑ ለቱሪስት መዳረሻ የሚሆኑ ዘርፈ ብዙ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ሀብቶች አሉ።

ይሁን እንጂ እነዚህን ሀብቶች በሚፈለገው ደረጃ ማልማት ባለመቻሉ ከዘርፉ በሚጠበቀው ልክ ጥቅም ማግኘት ሳይቻል መቆየቱን ገልፀዋል።

አሁን ላይ በገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት የሎጎ ሀይቅን ለማልማት እንቅስቃሴ መጀመሩን ጠቅሰው፤ ይህም የቱሪዝም ዘርፉን ከማነቃቃት ባለፈ ለዜጎች የስራ እድል በመፍጠር የጎላ ሚና እንዳለው አመልክተዋል።

ለስራው ስኬታማነት ተገቢው ድጋፍና እገዛ እንደሚደረግ ጠቅሰው፤ በአሁኑ ወቅትም ከአካባቢው ለሚነሱ አርሶ አደሮች የካሳ ክፍያ እየተከናወነ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል።

በተጨማሪም ለልማቱ አስፈላጊ የሆኑ ዝግጅቶች እየተከናወኑ እንደሚገኝ ሃላፊው አስታውቀዋል።

የአመራር አባላቱ ከጉብኝቱ በኋላ በሐይቅ ከተማ በ77 ሚሊዮን ብር የተገነቡ ፕሮጀክቶችን መርቀው አገልግሎት ያስጀምራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም