የአርሶ አደሩን ህይወት ከመቀየር እስከ ዓለም አቀፍ ተሞክሮ - ኢዜአ አማርኛ
የአርሶ አደሩን ህይወት ከመቀየር እስከ ዓለም አቀፍ ተሞክሮ
ግብርና በዓለም የኢኮኖሚ ግዙፍ ከሚባሉ ዘርፎች አንዱ ነው። በዓለም ላይ ለመኖር ምቹ ከሆነው የምድር ክፍል (Habitable land) ውስጥ ግማሹ ለግብርና ሥራ ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። ከዓለም ሕዝብ አንድ-አራተኛ የሚሆነው በግብርና ሥራ ተሰማርቶ ይገኛል።
እንደ ዓለም ባንክ መረጃ ከሆነ፤ ግብርናው በዓለም አጠቃላይ አገራዊ ምርት ውስጥ የ4 በመቶ ድርሻ ይይዛል። ይህ አኃዝ በተወሰኑ በማደግ ላይ በሚገኙ አገራት እስከ 25 በመቶ ይደርሳል።
ግብርና ከዓለም የወጪ ንግድ የ20 በመቶው እንዲሁም አገራት ከሚያስገቧቸው ምርቶች 16 በመቶ ገደማ ድርሻ እንዳለው አሃዛዊ መረጃዎች ያሳያሉ።
ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ ግብርና ዋነኛው የኢኮኖሚ መሠረት ነው። የግብርናው ዘርፍ ከአጠቃላይ አገራዊ ምርት (ጂዲፒ) የ40 በመቶ እና ከወጪ ንግዱ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነውን ድርሻ ይዟል።
አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ በግብርናው ሥራ ላይ የተሰማራ ነው። ዘርፉ በሚሊየኖች ለሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠረ ነው።
ኢትዮጵያ እምቅ የግብርና አቅም ያላትና ዘርፉ የሚፈልገውን ምቹ የአየር ንብረትና የአፈር ሁኔታ የያዘች አገር ናት።
ስንዴ ቁንጮው ሰብል
በዓለም የግብርና ታሪክ ውስጥ በዋናነት ከሚነሱ ምርቶች አንዱ ስንዴ ነው። የስንዴ ምርት የ10 ሺህ ዓመት ታሪክ ያለው መሆኑ ይነገራል።
ስንዴ በዓለም አቀፍ ደረጃ ብዙ ሰዎች የሚጠቀሙት የግብርና ምርት ሲሆን፤ 13 በመቶ ፕሮቲን የያዘው ይህ ሰብል የኃይል ሰጪነት አቅሙ ከፍተኛ የሚባል ነው።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ778 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን በላይ ስንዴ በየዓመቱ እንደሚመረት መረጃዎች ያመለክታሉ።
ሩሲያ በዓለም ትልቋ የስንዴ አምራች አገር ስትሆን በየዓመቱ ከ43 ሚሊየን ቶን በላይ ስንዴ በማምረት የምርቱን 24 በመቶ ገደማ ድርሻ ትይዛለች።
ካናዳ፣ አሜሪካ፣ ፈረንሳይ፣ ዩክሬን፣ አውስትራሊያ፣ አርጀንቲና፣ ካዛኪስታን፣ ሮማንያና ጀርመን ከሩሲያ በመቀጠል ከፍተኛ ስንዴ አምራች አገራት ናቸው።
እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2021 በወጣ አንድ ጥናት በዓለም ደረጃ በ220 ነጥብ 7 ሚሊየን ሄክታር መሬት ላይ እየተመረተ እንደሚገኝና ይኸውም ከሌሎች የምግብ ምርቶች እንደሚበልጥ ይገልጻል።
በዓለም በየዓመቱ 190 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን የስንዴ ንግድ ልውውጥ እንዳለ መረጃዎች ያሳያሉ።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የስንዴ ንግድ መጠን የሌሎች የሰብል ምርቶች የምርት ግብይት ተደምሮ ያለውን ይበልጣል።
የስንዴ ልማት በኢትዮጵያ
ስንዴ በኢትዮጵያ ከሚመረቱና ለግብይት ከሚውሉ የሰብል ምርቶች መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው።
ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ከፍተኛ ስንዴ አምራቾች አንዷ እንደሆነችና በአፍሪካ ከሚመረተው ስንዴ 20 በመቶ የሚሆነው ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚመረት መረጃዎች ያመለክታሉ።
ስንዴ በኢትዮጵያ በሚሸፍነው መሬት ስፋት በሦስተኛ እንዲሁም በሚሰጠው የምርት መጠን በሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደሚቀመጥም እንዲሁ።
በተለይ ባለፉት አምስት ዓመታት መንግሥት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማሳደግና ተግዳሮቶቹን ለመፍታት በግብርናው ዘርፍ ካደረገባቸው ሥራዎች አንዱ የስንዴ ልማት ነው።
መንግሥት መስኖን በመጠቀም ስንዴን በዓመት ሦስት ጊዜ ማምረት የሚቻልበትን መንገድ በመፍጠር የአገሪቱን ምርታማነት ለማሳደግ እየሰራ ይገኛል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት እያደገና በተለያዩ ክልሎች እየተስፋፋ በመምጣቱ ለስንዴ ልማት ጥቅም ላይ የሚውለው መሬት እያደገ መጥቷል።
የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት እያደገ መምጣቱ በቆላማ አካባቢዎች የሚገኙ አያሌ አርሶና አርብቶ አደሮች በሥራው ላይ እንዲሰማሩ በር ከፍቷል።
በ2016 በጀት ዓመት 3 ሚሊየን ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ለመሸፈን ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በዕቅዱ መሠረት በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ አምስት ወራት 2 ነጥብ 4 ሚሊየን ሄክተር መሬት ታርሶ የተዘጋጀ ሲሆን፤ 1 ነጥብ 9 ሚሊየን ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑ ተገልጿል።
ከበጋ ወቅት የመስኖ ስንዴ ልማት 117 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማግኘት መታቀዱን ሚኒስቴሩ ገልጿል።
የተያዘውን አገራዊ የመስኖ ስንዴ ልማት ዕቅድ ለማሳካት የአፈር ማዳበሪያ፣ የምርጥ ዘር፣ የውሃ መሳቢያ ሞተር ፓምፕ ካሉ ግብአቶች አቅርቦት ባሻገር የቴክኒክ ድጋፎችም የሚደረጉ መሆኑን ነው ሚኒስቴሩ ያስታወቀው።
ስንዴ ከመግዛት ለውጭ ገበያ ወደ ማቅረብ
ኢትዮጵያ ዓመታዊ የስንዴ ፍላጎቷ ከ107 ሚሊየን ኩንታል በላይ ነው። ይህንን ፍላጎቷን ለመሙላት ለዓመታት ከ700 ሚሊየን ዶላር እስከ 1 ቢሊየን ዶላር ለስንዴ ግዥ ወጪ ታደርግ ነበር።
ከዚህ ቀደም ከዓመታዊ የስንዴ ፍላጎቷ ከ25 እስከ 30 በመቶ የሚሆነውን ትሸፍን የነበረው ከውጭ በምትገዛው ስንዴ ነበር።
መንግሥት የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትን በማስፋትና ስንዴ በየዓመቱ የሚመረትበትን ወቅት በመጨመር ኢትዮጵያ የስንዴ ፍጆታዋን እንድትሸፍን በትኩረት ሲሰራ ቆይቷል።
በዚሁ መሠረት በ2014 ዓ.ም ኢትዮጵያ ከውጭ አገር ስንዴ ማስገባት አቆመች።
ኢትዮጵያ በስንዴ ልማት ያገኘችው ውጤት ከውጭ ማስገባትን ማስቆም ብቻ አልነበረም።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት ራስን መቻል ብቻ ሳይሆን ኤክስፖርት የማድረግ አቅም እንዳላት በመግለጽ ስንዴ ወደ ውጭ መላክ እንደሚገባ አቅጣጫ አስቀመጡ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስቀመጡት ሀገራዊ ግብ መሠረት ኢትዮጵያ የካቲት 5 ቀን 2015 ዓ.ም ወደ ውጭ የመላክ ተግባርን በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን በይፋ አስጀመረች።
የስንዴ ኤክስፖርቱ ኢትዮጵያ ገጽታዋን የሚለውጥ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ መግባቷን የሚያመላክት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ ገልጸው ነበር።
ኢትዮጵያ በ2015 ዓ.ም የአገር ውስጥ ፍጆታዋን ሸፍና 32 ሚሊየን ኩንታል ስንዴ ለውጭ ገበያ የማቅረብ አቅም እንዳላት ብሔራዊ የማክሮ ኢኮኖሚና የኤክስፖርት ኮሚቴ አረጋግጧል።
ኮሚቴው የአገራዊ የነፍስ ወከፍ ፍጆታና የአገሪቱን አጠቃላይ የምርት ሚዛን በማጥናት ከፍጆታ የሚተርፍ 32 ሚሊየን ኩንታል ስንዴ ወደ ውጭ መላክ እንደሚቻልም ገልጿል።
የረድኤትና ሌሎች የሀገር ውስጥ ድርጅቶች ከውጭ የሚገዙትን በሀገር ውስጥ እንዲተኩ በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል የ2 ነጥብ 9 ሚሊየን ኩንታል የውል ስምምነት በ2015 ዓ.ም ተፈርሟል።
ኢትዮጵያ በ2015 ዓ.ም ለኬንያ ስንዴ ለመላክ ስምምነት መፈራረሟም የሚታወስ ነው።
ጂቡቲ ከኢትዮጵያ ስንዴ መግዛት እንደምትፈልግ የጂቡቲ ግብርና ሚኒስትር መሐመድ አሕመድ አዋሌህ በ2015 ዓ.ም ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልፀዋል።
ጂቡቲ ኢትዮጵያ ከጀመረችው የስንዴ ልማት ብዙ ተሞክሮ እንደምትወስድም በወቅቱ ጠቁመዋል።
እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ግንቦት 2022 የቡድን ሰባት አገራት ሚኒስትሮች በጀርመን ባካሄዱት ስብሰባ ላይ የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት፣ ዶክተር አክንዊሚ አዲሲና ኢትዮጵያ ከዚህ በኋላ ስንዴ ከውጪ እንደማታስገባ ገልጸው ነበር።
እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 2021 ጀምሮ ኢትዮጵያ ከውጭ አለማስገባቷን የተናገሩ ሲሆን፤ ለሚቀጥለው ዓመት በ2 ሚሊየን ሄክታር ላይ ለማምረት ዕቅድ ስላላት ይህንን ምርት በ2023 ለጎረቤት አገራት ጂቡቲ እና ኬንያ ለመሸጥ ማሰቧን አመልክተዋል።
እንደ አሜሪካ ግብርና ቢሮ መረጃ በኢትዮጵያ የስንዴ ምርት ዘርፍ ትልቅ እመርታ እያሳየ እና ምርታማነቱ እየጨመረ ነው።
የአሜሪካ የግብርና ቢሮ ሪፖርት ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2022/2023 ዓመት ውስጥ 5 ነጥብ 7 ሚሊየን ቶን ስንዴ ታመርታለች ተብሎ እንደሚጠበቅ ተንብዮ ነበር።
የኢትዮጵያ መንግሥት ባለፉት ዓመታት የስንዴ ምርት እንዲያድግ የመስኖ ልማት፣ የግብርና ኤክስቴንሽን ድጋፍ በዘመናዊ መሳሪያ የታገዘ የእርሻ ሥርዓት እንዲዘረጋ እየሰራ መሆኑንና ግብዓቶች እያቀረበ እንደሚገኝ ቢሮው በወቅቱ ባወጣው መረጃ አስታውቋል።
ኢትዮጵያ ስንዴ ኤክስፖርት በማድረግ የጀመረችው ሥራና የበጋ መስኖ ልማት ስንዴ ሥራው በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሞክሮ መሆን ችሏል።
የስንዴ ኤክስፖርት መጀመሩ አርሶ አደሮች ከእጅ ወደ አፍ የአኗኗር ዘይቤ ተላቀው ወደ ሰፋፊ ልማት እንዲገቡና በታክስ ሥርዓቱ ውስጥ ተካተው የአገር ውስጥ ገቢን ከፍ ለማድረግ የበኩላቸውን እንዲወጡ የሚያስችል መሆኑ ታምኖበት እየተተገበረ ነው።
የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ለአርሶ አደሩ ይዞ የመጣው ዕድልና አማራጭ
የበጋ ስንዴ ልማት በኢትዮጵያ ከምርታማነቱ ባሻገር የሥራ ዕድል በመፍጠር አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል።
አርሶ አደሮች ከግብርና ባለሙያዎች የሚያገኙት ሙያዊ ምክር በስንዴ ልማት ውጤታማ እንዲሆን አስተዋፅዖ ማድረጉን ይገልጻሉ።
የድጋፍና ክትትሉ ሥራ አርሶ አደሩ ወደ ስንዴ ልማት ሥራ እንዲገባ ማስቻሉ ይገለጻል።
ከፍተኛ ጊዜ፣ ጉልበትና ወጪ የሚጠይቁ ምርቶችን በስንዴ በመተካት አዋጪና የተሻለ ምርት እያገኙበት እንደሆነም ይናገራሉ።
መረጃዎች እንደሚያመላክቱት በኢትዮጵያ ከ1 ሄክታር መሬት ላይ ከ3 ቶን በላይ ስንዴ ምርት ይገኛል።
አርሶ አደሩ በበጋ ስንዴ ልማቱ የኩታገጠም የአስተራረስ ዘዴን በመጠቀም የተሻለ ምርታማነትን እያገኘ ነው።
መንግሥት ስንዴን ጨምሮ ለተለያዩ የግብርና ምርቶች አርሶ አደሩ የሚፈልጋቸውን የምርጥ ዘርና ማዳበሪያ አቅርቦቶች እንዲሁም ቴክኖሎጂዎች በወቅቱ በማድረስ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።
አርሶ አደሩ ስንዴውን ማምረት ብቻ ሳይሆን እየተፈጠረለት ባለው የገበያ ትስስር የኢኮኖሚ ተጠቃሚ መሆን ችሏል።
መቋጫ
መንግሥት ስንዴ በስፋት መመረት አለበት በሚል ከበልግ እርሻ ባሻገር በጋ ላይም እንዲመረት ማድረጉ የአገር ውስጥ ምርትን ከመሸፈን አልፎ ኤክስፖርት ወደ ማድረግ ደረጃ መሸጋገር አስችሏል።
ይህ ውጤት ለኢትዮጵያውያን በምግብ ራስን የመቻልና ለሌሎች የመትረፍ ጉዞ በይቻላል መንፈስ እንዲያጠናክሩ ጉልበት የሚፈጥር ነው።
ለጎረቤቶቿና ለሌሎች አገሮች ደግሞ ተሞክሮ የሰጠ የትጋት ውጤት ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ ነው።
ኢትዮጵያ በስንዴ ልማት ዘርፉ የጀመረችው ሥራ የግብርና ዘርፉ በትክክለኛ አቅጣጫ ላይ እንደሚገኝ የሚያሳይ ነው።
ባለፉት ዓመታት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነት የተሰሩ የልማት ስራዎች የአርሶ አደሩን ሕይወት ከመቀየር ባለፈ ዓለም አቀፍ ተሞክሮ ሆነዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምግብ ዋስትና እና በተመጣጠነ የምግብ አቅርቦት ላሳዩት ርዕይ፣ አመራር እና ቁርጠኝነት፣ ብሎም ፈጣን፣ ተለዋዋጭ እና ፈታኝ በሆነው ከባቢያዊ ሁኔታ በስንዴ ምርት ራስን ለመቻል ለተከተሉት ፈጠራዊ መፍትሔ የተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት (ፋኦ) የከበረውን የፋኦ አግሪኮላ ሜዳልያ ሸልሟቸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ጊዜ ባደረጉት ንግግር በኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ አገራዊ ብልጽግናን እውን ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ረሃብን ሙሉ በሙሉ ከማስቀረት ባለፈ የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ብሄራዊ ብልጽግናን እውን ለማድረግ እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
በተለይም የግብርናው ዘርፍ ምርታማነት በሀገሪቱ ላለው 120 ሚሊዮን ህዝብ የማይተካ ሚና እንዳለው ገልጸው በዘርፉ በተከናወኑ የማሻሻያ ተግባራት የሚታረስ መሬት ምጣኔን ከ50 በመቶ በላይ ማሳደግ መቻሉን ጠቅሰዋል።
በልዩ ትኩረት ት የተጀመረው የመስኖ ስንዴ ልማት ለበርካታ አስርት ዓመታት ከውጭ በማስገባት ጥገኛ የሆንበትን ሂደት የለወጠ መሆኑን በማንሳት በስንዴ ልማት ላይ የተከተልነው ዘመናዊ የልማት ቴክኖለጂ ከስንዴ እጥረት በማላቀቅ ከፍተኛ የምርት ዕድገት አስገኝቷል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ለስንዴ ምርት የሚሆን ከፍተኛ የውሃና የመሬት አቅርቦት እንዲሁም የሰው ኃይል ያላት አገር በመሆኗ ይህንን ኃብት በሙሉ አቅም መጠቀም ከተቻለ ከዚህም በላይ ውጤታማ ሥራ መሥራት ይችላል።