ቀጥታ፡

ሰላምን  በዘላቂነት ለማጽናት በሚከናወኑ ተግባራት ተሳትፏችንን  እናጠናክራለን -የምዕራብና ማዕከላዊ ጎንደር ዞን ነዋሪዎች

መተማ ፤ጥር 19/2016 (ኢዜአ)፦ የአካባቢያችን ሰላም በዘላቂነት ለማጽናት በሚከናወኑ ተግባራት ተሳትፏችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ የምዕራብና ማዕከላዊ ጎንደር ዞን ነዋሪዎች ገለጹ።

የምዕራብ ጎንደር ቀጣና ኮማንድ ፖስት ከዞኖቹ ወረዳዎችና ቀበሌዎች ከተወጣጡ የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር በጸጥታና ሌሎች ወቅታዊ ሁኔታዎች ዙሪያ  በነጋዴ ባህር ከተማ ዛሬ ምክክር አካሄዷል። 

ነዋሪዎቹ በውይይቱ ላይ እንደገለጹት፤ የሰላምና የጸጥታ ጉዳይ በመንግስት ብቻ የሚከወን ባለመሆኑ  በአካባቢያቸው ሰላምን በዘላቂነት ለማስፈን ተሳትፏቸውን አጠናክረው ይቀጥላሉ።

የመተማ ወረዳ ነዋሪ አቶ እያዩ ተዋበ እንዳሉት፤ ሰላምና ጸጥታ በመንግስት ብቻ የማይጸና በመሆኑ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ በጋራ ሰላምን ለማስፈን ይተጋሉ።

ሌላኛው ከጭልጋ ወረዳ የመጡት የምክክሩ ተሳታፊ አቶ ሙላቴ  አየልኝ  በበኩላቸው፤ “የዞኑ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት በህገወጥ ድርጊት ሊስተጓጎል አይገባም “ ብለዋል።

 “አካባቢያችን  ለወጭ ንግድና ኢንዱስትሪ ግብዓት ለሚሆኑ ምርቶች ልማት ተመራጭ በመሆኑ ልማቱ በህገ ወጥ ድርጊቶች እንዳይስተጓጎል  በጋራ እንሰራለን “ ሲሉም አክለዋል።

“ከመንግስት የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ለአካባቢያችን ዘላቂ ሰላም መስፈን በጋራ እንሰራለን” ያሉት ደግሞ የአዳኝ አገር ጫቆ ወረዳ ነዋሪ አቶ ዳገት ከፋለ ናቸው።

“ወንጀለኞችን በማጋለጥና ለህግ በማቅረብ ለአካባቢው ጸጥታና ሰላም መጽናት ሀላፊነታችንን እንወጣለን “ ሲሉ ተናግረዋል።

የ503ኛ ኮር አዛዥና የምዕራብ ጎንደር ቀጣና  ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ብርጋዴር ጀኔራል መካሻ ጀምበር፤ በአካባቢው ሰላምን ለማጽናት እየተደረገ ባለ ጥረት ህዝቡ ተሳትፎውን አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በሁከትና ግጭት የራስን እኩይ ዓላማ ለማሳካት መሞከር ዴሞክራሲያዊ ሳይሆን የጥፋት መንገድ መሆኑን አመልክተው፤ ህዝቡ በዚህ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ቡድኖችን ለማስቆም ተሳትፎውን እንዲያጠናክር አስገንዝበዋል።

የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቢክስ ወርቄ በበኩላቸው፤ የአካባቢውን ሰላም በዘላቂነት ለማስጠበቅ የህዝቡ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

መንግስት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ በመቀበል የታጠቁ ቡድኖች ወደ ሰላም እንዲመጡ በማድረግ ሂደት ህብረተሰቡ ሀላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

በመድረኩ ላይ የፀጥታ አካላት አመራር አባላት፣ የዞንና የወረዳ ከፍተኛ አመራር አባላት፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ልዩ ልዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም