በኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ሀገራዊ ብልጽግናን እውን ለማድረግ እየተሰራ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ሀገራዊ ብልጽግናን እውን ለማድረግ እየተሰራ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ጥር 19/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ሀገራዊ ብልጽግናን እውን ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በምግብ ዋስትናና በተመጣጠነ የምግብ አቅርቦት ላሳዩት ርዕይ፣ የአመራር ቁርጠኝነት የተባበሩት መንግስታት የምግብ እና የግብርና ድርጅት (ፋኦ) የአግሪኮላ ሜዳልያ ሸልሟቸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በመድረኩ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር የዓለም ምግብ ና የእርሻ ደርጅት ያበረከተላቸውን የተከበረ ሜዳሊያ በፍጹም ትህትና መቀበላቸውን አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የተመጣጠነ ምግብ ተደራሽነትን እውን ለማድረግ ለሰራችው ስራ እውቅና በመሰጠቱ ደስታ እንደተሰማቸው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ረሃብን ሙሉ በሙሉ ከማስቀረት ባለፈ የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ብሄራዊ ብልጽግናን እውን ለማድረግ እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ በርካታ ያልተነኩ ጥሬ ሃብቶች፣ ተስማሚ የአየር ንብረትና ለስራ ትጉ የሆነ ወጣት እንዳላት ተናግረዋል።
እነዚህን ሃብቶች ታሳቢ በማድረግ የታሪክ አውራ የሆነችውን ሀገር ልማት ወደፊት ለማራመድ የመደመር ፍልስፍና ወሳኝ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ባለፉት አምስት ዓመታት በሁሉም ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራት ለሚቀጥለው ትውልድ መሰረት የሚጥሉ መሆኑንም አንሰተዋል።
ከአምስት ዓመት በፊት ይፋ በተደረገው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ቱሪዝም፣ ማዕድንና የኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን ቴክኖሎጂ ለዕድገት መሰረት መሆናቸው መለየቱን ጠቅሰዋል።
እነዚህ አምስት የኢኮኖሚ ምሰሶዎች ያልተነካ እምቅ አቅም ያላቸው መሆናቸውንም ተናግረዋል።
በተለይም የግብርናው ዘርፍ ምርታማነት በሀገሪቱ ላለው 120 ሚሊዮን ህዝብ የማይተካ ሚና እንዳለው በመናገር ሌሎቹም ለኢኮኖሚ ዕድገታችን መሳለጥ መዘውር ናቸው ብለዋል።
በግብርናው ዘርፍ በተከናወኑ የማሻሻያ ተግባራት የሚታረስ መሬት ምጣኔን ከ50 በመቶ በላይ ማሳደግ መቻሉን ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም አሁንም ለመታረስ ዝግጁ የሆነ ሰፊ የመሬት ሃብት መኖሩን ጠቁመዋል።
በግብርናው ዘርፍ ያለንን እምቅ አቅም አሟጠን ለመጠቀም የጀመርነውን ጥረት አጠናክረን ቀጥለናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለይም ከፍተኛ ዋጋ የሚያስገኙና ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ ተክሎችን ለማብቀል የጀመርነው ጥረት ተስፋ ሰጪ ነው ብለዋል።
ድርቅን የሚቋቋሙና የውኃ ፍጆታቸው አነስተኛ የሆኑ ተክሎችን ለማብቀል የተጀመረው ስራ አበረታች መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም የስንዴ፣ የጤፍ፣ የበቆሎና የገብስ ልማት ስራዎች ውጤታቸው በተጨባጭ እየታየ ነው ብለዋል።
በልዩ ትኩረት በመስኖ ልማት የጀመርነው የስንዴ ልማት ለበርካታ አስርት ዓመታት ከውጭ በማስገባት ጥገኛ የሆንበትን ሂደት የለወጠ ነው ሲሉም አክለዋል።
በስንዴ ልማት ላይ የተከተልነው ዘመናዊ የልማት ቴክኖሎጂ ከስንዴ እጥረት በማላቀቅ ከፍተኛ የምርት ዕድገት አስገኝቶልናል በማለት ስኬቱን በመድረኩ ለተገኙ እንግዶች አጋርተዋል።
ከድህነት ለመውጣት ያለንን የሰው ሃብት በመጠቀም ምርታማነትን ማሳደግ ይጠበቅብናል ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።
አምራች የሆነውን የሰው ሃብታችንን ለመጠቀም ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ መመደብ አለብን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለዚህ ደግሞ የሚታረስ መሬትን ከማስፋፋት ባለፈ በወተት፣ በስጋ፣ በዶሮ፣ በአሳና በማር ምርት ላይ በትኩረት እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።
እኤአ ከ2018 አንስቶ ከስምንት ባለነሱ የኢንቨስትመንት ከባቢ ጉዳዮች ላይ ማሻሻያ መደረጉን በመግለጽ የተቋማት ግንባታና የህግና መመሪያዎች ማሻሻያዎች የዚሁ አካል መሆናቸውን አስታውቀዋል።
ይህ ተግባር ኢትዮጵያን ለኢንቨስትመንት ተመራጭ አድርጓታል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የገጠሟትን ፈተናዎች በመቋቋም በተረጋጋ ሁኔታ ላይ ቆማ በዕድገት ወደፊት እየገሰገሰች መሆኗን በመጠቆም ይህም የልማት ግቧን ለማሳካትና ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እንዳስቻላት ተናግረዋል።
ባለሃብቶችም በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ አቅርበዋል።
በኢትዮጵያ የለውጥ ጉዞ ውስጥ ድጋፍ ያደረጉ የልማት አጋሮች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምስጋና አቅርበዋል።