የዓለማችንን አዳዲስና ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በአገልግሎት ላይ በማዋል ዲጂታል ኢትዮጵያን ዕውን እናደርጋለን - ኢትዮ -ቴሌኮም

ድሬዳዋ፤ጥር 19/2016 (ኢዜአ)፡- የዓለማችንን አዳዲስና ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በአገልግሎት ላይ በማዋል ዲጂታል ኢትዮጵያን ዕውን እናደርጋለን ሲሉ የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ ተናገሩ።

ዋና ስራ አስፈፃሚዋ ይህን የተናገሩት ትናንት ማምሻውን በድሬዳዋ የአምስተኛውን ትውልድ /5G/  ዘመናዊ የሞባይል ኔትወርክ አገልግሎት ከድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ ጋር በጋራ ባስጀመሩበት ወቅት ነው።

በድሬዳዋ የተካሄደው መርሃ ግብር ከወራት በፊት በአዲስ አበባ ፣ በአዳማና በጅግጅጋ ተግባራዊ የተደረገው የመጨረሻው ፋጣንና ዘመናዊ የአምስተኛው ትውልድ የሞባይል ኔትወርክ አገልግሎት ዲጂታል ኢትዮጵያን ዕውን የማድረጉ ሂደት መገለጫ ነው ብለዋል።

ወደ ተግባር የተሸጋገረው ዘመናዊው ቴክኖሎጂ  በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ አገር ለመገንባትና የዜጎችን አኗኗር ዘመናዊና ቀላል ለማድረግ እንደሚያስችልም ነው የገለፁት።

በተለይም ኢትዮጵያ በግብርናው፣ በጤናው፣ በትምህርት፣ በኢንዱስትሪ፣ በማዕድን፣ በአገልግሎትና በቱሪዝም ሴክተሮች የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ የጀመረቻቸው የብልጽግና ትልሞች በፍጥነትና በአነስተኛ ወጪ ዕውን እንዲሆኑ መሠረታዊ ሚና ያበረክታል ብለዋል።

እንደ ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ፍሬህይወት ገለፃ የአምስተኛው ትውልድ የሞባይል ኔትወርክ አገልግሎት የዲጂታል ኢኮኖሚን በመገንባት ረገድም ዘላቂና ቀጣይነት ያለው ዕድገት ለማስመዝገብ ያስችላል።

በተጨማሪም በፋይናንስ ሴክተር ውስጥ ስርነቀል ለውጥ ለማምጣትና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ስራዎች እንዲስፋፉ በማስቻል ዜጎች የስራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ መሠረታዊ አበርክቶ እንዳለው በማከል።


 

የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሀርቢ  ቡህ በበኩላቸው የ5ኛው ትውልድ የሞባይል ኔትወርክ አገልግሎት በከተማዋ የሚገኙትን ከ450 በላይ የአምራች ኢንዱስትዎችን ተደራሽ ያደርጋል።

የነፃ ንግድ ቀጣና እንዲሁም ከ45 ሺህ በላይ ነጋዴዎች ተወዳዳሪ በመሆን፣ ምርትና ምርታማነት በማሳደግ የተሻለ ዕድገት እንዲያስመዘግቡም ያግዛል ብለዋል።

በተጨማሪም   የአምስተኛው ትውልድ የሞባይል ኔትወርክ አገልግሎት መጀመር የአገራችንና የድሬዳዋን ሁለንተናዊ የብልፅግና ጉዞ ለማሳካት ወሳኝ ሚና ስላለው፤ ይህንን ሃብት በአግባቡ መጠበቅና መጠቀም የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት  ነው ብለዋል።

በ5ኛው ትውልድ የሞባይል ኔትወርክ ማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የድሬዳዋ አስተዳደር የካቢኔ አባላት፣ የድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጣና አመራር አባላት፣ ኢንቨስተሮች፣ የመንግስትና  የግል ተቋማት አመራር አባላትና ሌሎችም እንግዶች ተሳታፊ ሆነዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም