የአፍሪካ ዋንጫን በመሀል ዳኝነት  የመራችው ብቸኛዋ ሴት ዳኛ

3485

 

በይስሐቅ ቀለመወርቅ 

እንደ መነሻ፡- 

በእግር ኳስ ውድድሮች የመሃል ዳኝነቱን ቦታ በብዛት የሚይዙት ወንዶች ሲሆኑ፤ አሁን ላይ አልፎ አልፎ ሴቶች ትልልቅ የእግር ኳስ ጨዋታዎችን ሲዳኙ አስተውለናል።

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2022 በኳታር አስተናጋጅነት በተከናወነው 22ኛው የፊፋ የዓለም ዋንጫ፤ ፈረንሳዊቷ ስቴፋኒ ፍራፓርት፤ ኮስታሪካ እና ጀርመን ያደረጉትን ጨዋታ በመሀል ዳኛነት መርታለች።

በዚህም በወንዶች ዓለም ዋንጫ ታሪክ በመሀል ዳኝነት የእግር ኳስ ጨዋታን የመራች የመጀመሪያዋ ሴት በመሆን ታሪክ ሰርታለች ።

ዘንድሮ ደግሞ በኮትዲቯር አስተናጋጅነት እየተከናወነ በሚገኘው 34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ሞሮኳዊቷ ቦችራ ካርቡቢ፤ ውድድሩን እንዲመሩ ከተመረጡት 32 የመሀል ዳኞች መካከል ብቸኛዋ ሴት ናት።

በዚህም በውድድሩ በጊኒ ቢሳውና በናይጄሪያ መካከል የተከናወነውን ሦስተኛ የምድብ ጨዋታ፤ በመሀል ዳኝት በመምራት፤ ታሪክ ጽፋለች።

የሞሮኮ ዓለም አቀፍ ማኅበር የእግር ኳስ ዳኛ የሆነችው ቦችራ ካርቡቢ፤ በወንዶችም ሆነ በሴቶች አህጉራዊ የእግር ኳስ ውድድሮች ላይ በርካታ የመጨረሻ ምዕራፍ የእግር ኳስ ጨዋታዎችን ዳኝታለች።

34ኛው የአፍሪካ ዋንጫን ብቸኛ የሴት ዳኛ ሆና የመራችው ቦችራ ካርቡቢ ማናት?

ቦችራ ካርቡቢ በሞሮኮ ሰሜናዊ ክፍል በምትገኘው "ታዛ" ከተማ፤ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1987 ተወለደች።

የዘር ግንዷ በሰሜን ምሥራቅ ሞሮኮ ከሚገኙት ሪፊያን ከሚባሉት የበርበር ጎሳ ዝርያ ካላቸው ሕዝቦች የሚመዘዝ ሲሆን፤ ለቤተሰቦቿ አምስተኛና የመጨረሻ ልጅ ነች።

ገና በልጅነቷ ለእግር ኳስ ፍቅር ያደረባት ቦችራ ካርቡቢ፤ ኳስ መጫወት የጀመረችው በአንድ ትንሽ የወጣቶች ቡድን ውስጥ ነበር። 

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2001 በተወለደችበት ከተማ "ታዛ"፤ ለወንዶችና ለሴቶች የእግር ኳስ ዳኝነት ሥልጠና የሚሰጥበት ትምህርት ቤት ተከፈተ ።

ይኼ ትምህርት ቤት ቀልቧን የሳበው ቦችራ፤ ሥልጠናውን መውሰድ ጀመረች።

"እግር ኳስን እወዳለሁ፤ ራሴንም ላስተምር ፈለኩ።ለምን አላደርገውም ብዬ ፍላጎቴን በመከተል የእግር ኳስ ጨዋታን ደንብ መማር ጀመርኩ" ስትል የእግር ኳስ ዳኝነት ትምህርት የጀመረችበትን ጊዜ ታስታውሳለች።

ይኼ ድርጊቷ ካልተዋጠላቸውና፤ በበጎ ጎኑ ካልተመለከቱት ውስጥ ደግሞ፤ ወንድሞቿ ቀዳሚዎች ነበሩ።

"በምኖርበት ከተማ አንድ ሴት አጭር ቁምጣ ለብሳ ከወንዶች ጋር ሥልጠና ስትወስድ መታየቷ፤ እንደ አሳፋሪ ድርጊት ስለሚታይ መነጋገሪያ ሆኜ ነበር" ትላለች።

የቦችራ ካርቡቢ የዳኝነት ጉዞ

እንደ አውሮፓውያን ቆጣጠር በ2007፤ ሞሮኮ ብሔራዊ የሴቶች እግር ኳስ ሻምፒዮናን ጀመረች።

ይህ መሆኑ ቡችራ ካርቡቢ ብሔራዊ ዳኛ እንድትሆን ዕድል የፈጠረላት ሲሆን፤ መኖሪያዋንም  ከትውልድ ሥፍራዋ "ታዛ" ወደ ሞሮኮ ሌላኛዋ ከተማ "ሚከንስ" እንድትቀይር አደረጋት።

"ይህን ዕድል ማግኘቴ ቤተሰቦቼ እንዲረዱኝና ሙያዊ ለሆነ ጉዳይ እንደምሄድ እንዲያምኑ አድርጓቸዋል" በማለት የዳኝነት ሙያዋን በመጨረሻ እንደተቀበሉት ታስረዳለች።

በሚከንስ ከተማ በእግር ኳስ ዳኝነት ሥልጠና ላይ እያለች፤ አንድ ቀን አባቷ መጥቶ እንደተመለከታትና፤ ወንድሞቿ ምርጫዋን ሊያከብሩላት እንደሚገባ እንደነገራቸውም ገልፃለች።  

የ19 ዓመት ወጣት እያለችም፤ በሞሮኮ የሴቶች አንደኛ እና ሁለተኛ የሊግ ውድድር በመዳኘት፤ የዳኝነት ሥራዋን አንድ ብላ ጀመረች።

ይህ ከሆነ ከ10 ዓመት በኋላ፤ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2016 ደግሞ፤ ዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ዳኛ በመሆን ራሷን ወደ ሌላ ምዕራፍ አሸጋገረች። 

ከሁለት ዓመት በኋላም በ2018 በጋና አስተናጋጅነት በተከናወነው የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ፤ በዛምቢያና በኢኳቶሪያል ጊኒ መካከል የተደረገውን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት አጫወተች።

ይህም በአህጉራዊ የውድድር መድረክ ለመጀመሪያ ጊዜ በመሀል ዳኝነት ያጫወተችው ጨዋታ ሆኖ ተመዘገበላት።

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2020፤ "ቦቶላ" እየተባለ በሚጠራው በሞሮኮ የወንዶች ከፍተኛ የሊግ ውድድር ላይ በመሀል ዳኝነት በመዳኘት፤ የመጀመሪያዋ ሴት ሆነች ።

ከአንድ ዓመት በኋላም በካሜሮን አስተናጋጅነት በተከናወነው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ፤ ሴኔጋልና ግብፅ ባደረጉት የፍፃሜ ጨዋታ የቫር ዳኛ (video assistant referee) በመሆን ሰርታለች።

ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊትም የሞሮኮ የንጉሱ ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታን በመዳኘትም ቀዳሚዋ ሴት ናት።

አሁን ላይ እየተከናወነ ባለው 34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ወድድርም፤ በጊኒ ቢሳውና በናይጄሪያ መካከል የተከናወነውን ሦስተኛ የምድብ ጨዋታ በመሀል ዳኝት በመምራት፤ የመጀመሪያዋ ሰሜን አፍሪካዊት የአረብ ሴት ሆናለች።

ቡችራ ካርቡቢ ከእግር ኳስ ዳኝነት ሥራዋ በተጨማሪ፤ የፖሊስ ኦፊሰር በመሆን ሀገሯን እያገለገለች ትገኛለች።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም