የሥጋ ደዌ ተጠቂዎችን በማህበራዊና ኢኮኖሚ ዘርፍ ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ የተከናወኑ ስራዎች ውጤት እያሳዩ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሥጋ ደዌ ተጠቂዎችን በማህበራዊና ኢኮኖሚ ዘርፍ ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ የተከናወኑ ስራዎች ውጤት እያሳዩ ነው
ሐረር ፤ ጥር 19/2016 (ኢዜአ)፡- የሥጋ ደዌ ተጠቂዎችን በማህበራዊና ኢኮኖሚ ዘርፍ ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ የተከናወኑት ተግባራት ውጤት ማሳየታቸውን የኢትዮጵያ የስጋ ደዌ ተጠቂዎች ብሔራዊ ማህበር ገለጸ።
የስጋ ደዌ ቀን በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ25ኛ ጊዜ በሐረር ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።
የኢትዮጵያ የስጋ ደዌ ተጠቂዎች ብሔራዊ ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ከፍያለው በቀለ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት በስጋ ደዌ ተጠቂዎች ላይ ቀደም ሲል ይደርስ የነበረው መገለል ሙሉ ለሙሉ ባይቀረፍም ካለፉት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር ለውጥ አለው።
የስጋ ደዌ ተጠቂዎች ከጥገኝነት ተላቀው የራሳቸውን ህይወት መምራት እንደቻሉ ማየታቸውን ገልጸው፤ በዚሁም በተከናወኑት ተግባራት ውጤት መታየቱን አክለዋል።
ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ማደግ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ መጨመር እንደ አንዱ ምክንያት አንስተው፤ መንግስት ትኩረት የሰጠበት ሁኔታም ለውጤቱ መሻሻል አስተዋጽኦ ማድረጉን አመልከተዋል።
የስጋ ደዌ ተጠቂዎችን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት እንዲሁም የሚደርስባቸው መድሎና መገለል ሙሉ ለሙሉ ለመቅረፍ አሁንም በርካታ ተግባራት መከናወን እንዳለበትም አልሸሸጉም።
ማህበሩም ተልዕኮውን ለማሳካት ከመንግስት፣ ከባለድርሻ አካላትና ከሌሎች ጋር እየሰራ እንደሚገኝ የጠቆሙት አቶ ከፍያለው፤ ይህም ስራ በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ ተናግረዋል።
በዓሉን ስናከብር ማህበረሰቡ ለስጋ ደዌ ተጠቂዎች ሁሉን አቀፍ ምላሽ መስጠት ይገባል ያሉት ደግሞ በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ አሳልፈው አመዲን ናቸው።
የስጋ ደዌ ተጠቂዎችን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት የሚያጎለብቱ ስራዎችም መጠናከር ይገባቸዋል ሲሉም ተናግረዋል።
የሐረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ሮዛ ኡመር በበኩላቸው ብሔራዊ በዓሉ የስጋ ደዌ ተጠቂዎች መብትና ጥቅም የሚጠናከርበትና በሽታውን ለማጥፋት በጋራ የምንመክርበት ነው ብለዋል።
እንዲሁም ህብረተሰቡ ለስጋ ደዌ ህሙማን የሚያደርገውን ድጋፍና ትብብር ለማጠናከር የሚያግዝ መሆኑንም አመልክተዋል።
በክልሉም በሽታው የሚያስከትለውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ለማቃለል የህክምና አሰጣጥ ስርዓቱ እንዲጠናከር ሆኗል፤ በተከናወነው ስራም ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል።
ቀኑን ምክንያት በማድረግም በትናንትናው ዕለት የእግር ጉዞ በከተማው ተካሂዷል።
ዛሬ በተካሄደው የፓናል ውይይት ላይ የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ የአመራር አባላት፣ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች፣ የስጋ ደዌ ተጠቂ ዜጎች፣ የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል።
የዘንድሮ የስጋ ደዌ ተጠቂዎች ቀን በዓል እየተከበረ ያለው "የስጋ ደዌ በሽታን አንዘንጋው" በሚል መሪ ሃሳብ ነው።