የ2024 ፓሪስ ኦሎምፒክ ሀገር አቀፍ የችቦ ቅብብሎሽ በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ ተካሄደ - ኢዜአ አማርኛ
የ2024 ፓሪስ ኦሎምፒክ ሀገር አቀፍ የችቦ ቅብብሎሽ በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ ተካሄደ
መቀሌ ፤ ጥር 19/2016 (ኢዜአ)፦ የ2024 ፓሪስ ኦሎምፒክ ሀገር አቀፍ የችቦ ቅብብሎሽ የማስጀመሪያ መርሃ ግብር በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ ዛሬ ተጀመረ።
በመጪው ሐምሌ ወር 2016 ዓ.ም ለሚካሄደው 33ኛው የፓሪስ ኦሎምፒክ በማህበረሰቡ ዘንድ ከወዲሁ መነቃቃት መፍጠርን ዓላማ ያደረገ የችቦ ቅብብሎሽ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ረዳት ኮሚሽነር አትሌት ደራርቱ ቱሉ አስጀምረዋል።
አትሌት ደራርቱ በወቅቱ እንደተናገሩት የኦሎምፒክ የችቦ ቅብብሎሽ መርሃ ግብር በሀገር አቀፍ ደረጃ በትግራይ ክልል መቀሌ በይፋ ተጀምሯል።
ቀጣይ ተረኛው ክልል የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አትሌቲክስ ፌደሬሽን ችቦውን ተረክቧል።
የኦሎምፒክ ችቦው ወደ ሁሉም ክልሎች ጉዞ ካደረገ በኋላ ሐምሌ 06 ቀን 2016ዓ.ም በአዲስ አበባ የጉዞ ፍፃሜውን እንደሚያገኝ ረዳት ኮሚሽነር አትሌት ደራርቱ ተናግረዋል።
"ኢትዮጵያን በዓለም አደባባይ ያስጠሩ በርካታ አትሌቶች ከትግራይ ክልል ወጥተዋል" ያሉት ረዳት ኮሚሽነሯ፤ በቀጣይም ተተኪዎችን ለማውጣት ከክልሉ ስፖርት ኮሚሽን ጋር ፌዴሬሽኑ በቅርበት ይሰራል ብለዋል።
ኦሎምፒክ ሰላም፣ ፍቅርና አንድነት የሚንፀባረቅበት በመሆኑ የኦሎምፒክ ችቦው በመላው ሀገሪቷ ሲዘዋወርም የኢትዮጵያን አንድነት የምናጠናክርበት መሆን አለበት ሲሉም ገልጸዋል።
የኦሎምፒክ ችቦውን ከትግራይ ክልል የተረከቡት የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሰይድ አልበሽር በበኩላቸው የችቦ ቅብብሉን ከትግራይ ክልል ልምድ ወስደን በድምቀት ለማክበር ተዘጋጅተናል ብለዋል።
በመርሃ ግብሩ የተለያዩ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንና የክልል አመራር አባላት በተገኙበት የኦሎምፒክ ችቦውን በመያዝ የእግር ጉዞ ተደርጓል፤ የተለያዩ ስፖርታዊ ክንውኖችም ተስተናግዶበታል።