ቀጥታ፡

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በሀገረ መንግስትና በትውልድ ግንባታ ዙሪያ የሚሰራውን ስራ ሊያጠናክር ይገባል - ዶክተር ለገሰ ቱሉ

አዲስ አበባ፤ ጥር 19/2016 (ኢዜአ)፡- ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በሀገረ መንግስትና በትውልድ ግንባታ ዙሪያ የሚሰራውን ስራ ሊያጠናክር እንደሚገባ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ አመለከቱ።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አዲስ ያስገነባው ፋና ላምሮት ስቱዲዮ የመንግሥት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት በይፋ ተመርቋል፡፡

በስነ ስርአቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ መገናኛ ብዙሃን ለሰላምና ለዲሞክራሲ እሴቶች ግንባታ ትልቅ ሚና አላቸው ብለዋል፡፡

ፋና ብሮድካስቲንገግ ኮርፖሬት በሀገረ መንግስት እና ትውልድ ግንባታ ዙሪያ አበረታች ስራዎች ማከናወኑን ጠቁመው በቀጣይም አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በኢትዮጵያ በርካታ ባህሎች፣ ቋንቋዎችና እሴቶች መኖራቸውን ጠቅሰው እነዚህን እሴቶች በማጎልበት ህዝቦችን ለማስተሳሰር እንዲውሉ መገናኛ ብዙሃን ሚናቸው ሊጎላ ይገባል ብለዋል፡፡

መንግሥት መገናኛ ብዙሃን እንዲጠናከሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል፡፡


 

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሀመድ እድሪስ በበኩላቸው ሀሰተኛ መረጃና የጥላቻ ትርክት ትልቅ ፈተና መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ፈተናዎቹ የበዙት መገናኛ ብዙሃን ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃ ተደራሽ በማድረግ በኩል ክፍተት ስላለባቸው በመሆኑ ይህንኑ ክፍተት ለመድፈን አበክረው ሊሰሩ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በሀገሪቱ በተለያዩ መልኮች በሚሰራጩ የጥላቻ ንግግሮችና ሀሰተኛ መረጃዎች የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዝም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም