ቀጥታ፡

በክልሉ የማህበረሰቡን ባህልና ዕሴት መሰረት አድርጎ በተከናወነ የሰላም ግንባታ ሥራ ውጤት መገኘቱ ተገለጸ

ሚዛን አማን ፤ጥር 19/2016(ኢዜአ)፦  በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የማኅበረሰቡን ባህልና እሴት መሰረት አድርጎ በተከናወነ የሰላም ግንባታ ሥራ ሰላምን በማረጋገጥ ወደልማት መገባቱን የክልሉ የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ፀጋዬ ማሞ ተናገሩ።

የሸኮ ማኅበረሰብ "ቲከሻ ቤንጊ" የዘመን መለወጫ በዓል በክልሉ ቤንች ሸኮ ዞን ሸኮ ወረዳ ተከብሯል።

በበዓሉ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት አቶ ፀጋዬ ማሞ ለክልሉ አስተማማኝ ሰላምና ልማት የህዝቦችን የእርስ በእርስ ትስስር ማጠናከር ላይ በትኩረት እየተሠራ ነው።

ለእዚህም ማኅበረሰቡ ያሉትን የሰላምና የአብሮነት ባህልና እሴቶች አውጥቶ በመጠቀም በክልሉ ግጭት የነበረባቸው አካባቢዎች ወደ ልማት እንዲገቡ ለማድረግ መቻሉን ነው የገለጹት

የቲከሻ ቤንጊ በዓል የዚህ ተግባር ትሩፋት መሆኑን ገልጸው፣ የሸኮ ማኅበረሰብ ጠብቆ ባቆየው ባህልና ታሪክ የሰፈነውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ ለሚያጋጩ ሳይሆን ለልማት ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የተገኘውን ሰላም በማስቀጠል ክልሉ ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ሀብት አልምቶ ለማደግና መለወጥ በጋራ መቆም እንደሚገባም አቶ ፀጋዬ አመላክተዋል።

አሁን የአካባቢው ትልቁ አጀንዳ ድህነትን ለማጥፋት ልማትና ዕድገትን ማረጋገጥ መሆኑንም ጠቅሰዋል።


 

የክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ፋንታሁን ብላቴ በበኩላቸው ባህል ወንድማማችነት የሚያጠናክር ጠንካራ ኃይል ስላለው መንከባከብና ማሳደግ እንደሚገባ ገልጸዋል።

የቲከሻ ቤንጊ በዓል ከዘመን መለወጫ በዓልነት ባሻገር በውስጡ ቱባ የሆኑ የሰላም፣ የልማትና የአንድነት እሴት ያለው በመሆኑ ቢሮው በዓሉ እንዲጎለበት በጥናት ላይ የተመሠረተ ሥራ ይሰራል ብለዋል። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም