በኢትዮጵያ ባሉት ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጮች በርካታ አገራት ለመሰማራት ፍላጎት አሳይተዋል - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ባሉት ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጮች በርካታ አገራት ለመሰማራት ፍላጎት አሳይተዋል
አዲስ አበባ ፤ጥር 19/ 2016 (ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ ባሉት ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጮች በርካታ አገራት ለመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው ኢትዮጵያን በተለያዩ አገራት የወከሉ አምባሳደሮች ተናገሩ።
በተለያዩ የአለም አገራት ኢትዮጵያን የወከሉ አምባሳደሮች በሀገሪቱ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል፡፡
የልማት እንቅስቃሴዎቹም ለዓለም አቀፍ የገበያ ትስስር አበርክቷቸው የላቀ መሆኑን አምባሳደሮቹ ተናግረዋል።
በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር ለኢዜአ እንደገለጹት በውጪ ጉዳይ ፖሊሲ ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች መካከል የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ አንዱና ዋነኛው ነው።
ይህን ለማሳካትም አምባሳደሮቹ በተመደቡባቸው አገራት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ ፍላጎት መሰረት በማድረግ ትስስር ለመፍጠርና አገራቱ ያላቸውን እምቅ አቅም ወደ ኢትዮጵያ እንዲያስገቡ እየሰሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ምርትና ምርታማነትን የሚጨምሩ ኢንቨስትመንቶችን መሳብ ዋናው ጉዳይ መሆኑን ያስረዱት አምባሳደሩ ፓኪስታን በግብርና ፣ በኬሚካል ኢንዱስትሪ፣ማኑፋክቸሪንግና በፋርማሲ ዘርፎች ትልቅ አቅም እንዳላት አስረድተዋል።
በዘርፉ የካበተ ልምድ ያላቸው የፓኪስታን አልሚዎችም በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን በማስታወስ የተጀመሩ ጥረቶች ዓለም አቀፍ የገበያ ትስስርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ለመፍጠር በእጅጉ የሚያግዙ እንደሆነም አክለዋል።
ፓኪስታን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ጽኑ አቋም ያላት ሲሆን ባለፈው አመት በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ 80 ባለሃብቶች መምጣታቸውን ተናግረዋል፡፡
በብራሰልስ የቤሉክስ አገራት ምክትል ሚሲዮን መሪ አምባሳደር ሻሜቦ ፊታሞ በበኩላቸው በአውሮፓ አገራት ያሉ አልሚዎች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው አንስተዋል።
ለዚህም በአገሪቱ ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮችን የማስተዋወቅና ሁኔታዎችን የማመቻቸት ስራ እያከናወኑ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።
ቀደም ሲል የነበሩትን ጨምሮ በአዳዲስ ዘርፎች የሚሰማሩ አልሚዎች ከዚህ ወር ጀምሮ በስፋት ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡ አምባሳደር ሻሜቦ አክለዋል።
በጃፓን የኢትዮጵያ አምባሳደር ዳባ ደበሌ በበኩላቸው ጃፓን በቴክኖሎጂ ውጤቶች የተሻለ አቅም ስላላት በኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ እውቀት ሽግግር ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ ያላትን የግብርና፣ የማዕድንና ኢነርጂ ሃብቶች በማስተዋወቅ የጃፓን ኢንቨስተሮች መጥተው እንዲያለሙ ጥረት እያደረጉ መሆኑን አንስተዋል።