ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በፓሪስ ኦሎምፒክ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ዝግጅት እያደረገች መሆኑ ተመለከተ

መቀሌ ጥር 18/2016(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በቀጣዩ ፓሪስ ኦሎምፒክ ካለፉት የኦሎምፒክ ውድድሮች የተሻለ ውጤት ለማስመዘገብ ዝግጅት እያደረገች መሆኑ ተመለከተ።

በኦሎምፒኩ ውጤታማ ለመሆን የሚያግዙ ሀሳቦችን ለማሰባሰብ የተዘጋጀ ሲምፖዚዬም ዛሬ በመቀሌ ከተማ ተካሂዷል። 

በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ አስተናጋጅነት የተካሄደው ሲምፖዚዬም በስፖርተኞችና በኅብረተሰቡ ዘንድ መነቃቃትን ለመፍጠር ያለመ እንደሆነም ተገልጿል። 

በኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ የቴክኒክ ኮሚቴና የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ  ቢልልኝ መቆያ ኢትዮጵያ በፓሪሱ ኦሎምፒክ የተሻለ ውጤት እንድታስመዘግብ የንቅናቄ መድረክ እየተዘጋጀ መሆኑን  ገልጸዋል። 

የመጀመሪያው የንቅናቄ መድረክ ዛሬ በብስክሌት ውድድርና በስፖርት ሲምፖዚዬም በመቀሌ ከተማ መካሄዱን  አስታውቀዋል። 

''በኦሎምፒክ መድረክ ኢትዮጵያን ያስጠሩ ስፖርተኞች ከትግራይ ክልል ወጥተዋል'' ያሉት አቶ ቢልልኝ፣ በቀጣዩ ኦሎምፒክ  አገርን ወክለው የሚሳተፉ ብቃት ያላቸው አትሌቶችና ብስክሌተኞች እንደሚኖሩ  እምነታቸውን ገልጸዋል። 

የትግራይ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ተክላይ ፈቃዱ በክልሉ የተጀመረው የኦሎምፒክ ንቅናቄ ለፓሪስ ኦሎምፒክ ብቻም ሳይሆን፤ ተቀዛቅዞ ለቆየው የክልሉን ስፖርት እንቅስቃሴ ለማነቃቃት ያግዛል ብለዋል። 

የስፖርት መሠረተ ልማትን መልሶ ለመገንባትና ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት የሁሉም አካላት ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል። 

የትግራይ ክልል ስፖርት ማህበራት ፕሬዚዳንት ዶክተር ከሳቴ ለገሠ በወቅቱ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፍ ከክልሉ የወጡ ስፖርተኞች ለኢትዮጵያ ስፖርት እድገት ከፍተኛ ሚና መጫወታቸውን ገልጸዋል። 

''በተለይም በአትሌቲክስና በብስክሌት ስፖርት የወጡት ስፖርተኞች የኢትዮጵያን ስም በዓለም አደባባይ አስጠርተዋል'' ብለዋል

የክልሉን ስፖርት ወደ ነበረበት በመመለስ ኢትዮጵያን የሚያስጠሩ ስፖርተኞች ለማፍራት የስፖርት መሰረተ ልማትን መልሶ መገንባትና የስፖርት አደረጃጀቱን መልሶ ማቋቋም እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል። 

በሲምፖዚዬሙ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ አመራር አባላት፣ የብሔራዊ ስፖርት ፌዴሬሽኖች ፕሬዚዳንቶች፣የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ተወካዮች፣የክለብ አሰልጣኞችና አትሌቶች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም