ቀጥታ፡

አገልግሎቱ ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው መጻሕፍትን በጋሞ ዞን ለሚገኙ ለተለያዩ ተቋማት አበረከተ

አርባ ምንጭ ፤ጥር 18/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ቤተ-መጻሕፍትና ቤተ-መዛግብት አገልግሎት ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው መጻሕፍትን በጋሞ ዞን ለሚገኙ ለተለያዩ ተቋማት አበረከተ።

የኢትዮጵያ ቤተ-መጻሕፍትና ቤተ-መዛግብት አገልግሎት ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የንባብ ሳምንት መርሃ-ግብር በአርባ ምንጭ ከተማ እየተካሄደ ነው።

በአገልግሎቱ የአብያተ መጻሕፍት አገልግሎት መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ያሬድ ተፈራ፣ የንባብ ባህልን ለማሳደግ አገልግሎቱ የተለያዩ ተግባራት እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።

ከዚህ ውስጥ አንዱ የንባብ ሳምንት ማዘጋጀት መሆኑን ጠቅሰው በአርባ ምጭ ከተማ የተዘጋጀው የንባብ ሳምንት ፕሮግራም ዓላማው የንባብ ባህልን በማሳደግ ዜጎች ለሀገሪቱ ዕድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት እንዲችሉ መሆኑን አስረድተዋል።

ከዚህ መርሃ ግብር ጎን ለጎን ከ1 ነጥብን 3 ሚሊዮን ብር በላይ  የሚገመት መጻህፍትን በጋሞ ዞን ለሚገኙ የተለያዩ ተቋማት ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።

ድጋፍ የተደረገላቸው ተቋማት በአርባ ምንጭ ከተማ እና ጨንቻ ዙሪያ ወረዳ የሚገኙ የተለያዩ ወጣት ማዕከላት፣ የህዝብ ቤተ-መጻሕፍት፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም ማረሚያ ተቋማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ታስቦ መሆኑን ገልጸዋል።

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲና በአከባቢው የሚገኙ የትምህርትና አስተዳደር አካላት ለሀገርና ትውልድ ግንባታ ታስቦ የተበረከቱ መጻሕፍት የአከባቢውን ማህረሰብ የንባብ ባህል በሚያሳድግ መልክ እንዲነበቡ በማድረግ የበኩላቸውን እንዲወጡ አቶ ያሬድ ተፈራ አሳስበዋል።


የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ዳምጠው ዳርዛ በበኩላቸው ''የሀገራችን ዕድገትና ስልጣኔ ሊረጋገጥ የሚችለው የንባብ ባህላችን ማሳደግ ስንችልና በርትተን ስንሰራ ነው'' ብለዋል።

የሚያነብ ዜጋ የተሻለ ዕውቀትና ግንዛቤ የሚኖረው በመሆኑ ለሀገር ዕድገት ከፍ ያለ አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚችል ጠቅሰው ዩኒቨርሲቲው ባቋቋመው የባህልና ቋንቋ ምርምር ማዕከል በመታገዝ የዜጎች የንባብ ባህል በማዳበር ለሀገር ዕድገት የበኩላቸውን እንዲወጡ በትኩረት እንሚሰራ ጠቁመዋል።


በአርባ ምንጭ ከተማ የተዘጋጀው የመጻህፍት አውደ ርዕይና የንባብ ሳምንት መርሃ-ግብር የአከባቢውን ማህበረሰብ የሚያነቃቃ መሆኑን የተናገረው ደግሞ የፕሮግራሙ ተሳታፊና የጫሞ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ9ኛ ክፍል ተማሪ ሚኪያስ ድልነሳው ነው።

በትምህርት ከሚገኘው ዕውቀት በተጓዳኝ የንባብ ባህልን ማሳደግ በስብዕናም ጭምር ለማደግ ወሳኝ መሆኑን ተናግሯል።

“አርባ ምንጭ ታንብብ” በሚል መሪ ሃሳብ ለአርባ ምንጭና አከባቢዋ የተዘጋጀው መርሃ-ግብር ለአራት ቀናት እንደሚቆይ ተገልጿል።

በዚህም የመጻህፍት አውደ ርዕይ፣ የመጻህፍት ሽያጭ እንዲሁም በመጻሕፍት፣ በሰነድና መዛግብት አስተዳደር ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እንደሚደረግ ተመላክቷል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም