ቀጥታ፡

የዕዳና የኃብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን ከተረከበው 400 ቢሊየን ብር ዕዳ እስካሁን 45 ቢሊየን ብር መክፈሉን ገለጸ

አዲስ አበባ፤ ጥር 18/2016(ኢዜአ)፦  የዕዳና የሃብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን ከተረከበው 400 ቢሊየን ብር ዕዳ እስካሁን 45 ቢሊየን ብር መክፈሉን አስታወቀ።

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ባለአደራ ቦርድ የተረከባቸውን ንብረቶች በመሸጥ 100 ሚሊየን ብር ገቢ ማግኘቱንም ኮርፖሬሽኑ ገልጿል።

የዕዳና የኃብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን ከፍተኛ የዕዳ ጫና ያለባቸውን ሰባት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የዕዳ ጫና ለማቋቋምና ኃብት ለማስተዳደር የተቋቋመ ነው።

በዚህም መሠረት ኮርፖሬሽኑ እያከናወናቸው ያሉ ሥራዎችን በተመለከተ የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሙሉዓለም ጌታሁን ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

በ2012 ዓ.ም. ሰባት የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ከፍተኛ የዕዳ ጫና ለማቃለል የሚያስችል ጥናት በማድረግ ካለባቸው 780 ቢሊየን ብር ዕዳ 570 ቢሊየን ብሩን መክፈል እንደማይችሉ መረጋገጡን አንስተዋል።

በዚህም ኮርፖሬሽኑ እስካሁን ባለው ከ570 ቢሊየን ብር 400 ቢሊየኑን ብር መረከቡን ገልጸው፤ በተለያዩ አማራጮች በመክፈል ላይ ነው ብለዋል።

ከመንግሥት የልማት ድርጅቶች በሚመደብለት የትርፍ ድርሻ፣ ከፕራይቬታይዜሽን፣ በራሱ በሚያደርጋቸው የንግድ ሥራዎችና ሌሎች የፋይናንስ ምንጮች በሚያገኘው ገንዘብ ዕዳውን የሚከፍል መሆኑንም ገልፀዋል። 

ኮርፖሬሽኑ በ2014 በጀት ዓመት ወደ ሥራ መግባቱን አስታውሰው፤ ከተረከበው 400 ቢሊየን ብር ዕዳ እስካሁን 45 ቢሊየን ብር መክፈሉን ተናግረዋል።

ዕዳውን ለመክፈል ዘላቂ የፋይናንስ ምንጭ ማመቻቸት አስፈላጊ በመሆኑ ባለፈው ዓመት የብድር ክፍያ ስትራቴጂ እንዲዘጋጅ መደረጉንም ጠቁመዋል።

ለዚህም የተለያዩ የልማት ድርጅቶችን የማቀናጀትና የአሠራር ሥርዓቶችን በመቅረፅ ላይ እንገኛለን ነው ያሉት።

ኮርፖሬሽኑ የቀድሞ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ባለአደራ ቦርድን ተረክቦ እንዲያስተዳድር መደረጉን አንስተው፤ እስካሁን ባለው የቦርዱን ንብረቶች በመሸጥ 100 ሚሊየን ብር ወደ ኮርፖሬሽኑ ገቢ መደረጉንም ገልፀዋል።

የቦርዱን የመሬት ይዞታዎችና ህንፃዎች ስም ለማዞርም እየተሰራ ነው ብለዋል።

ኮርፖሬሽኑን ለማደራጀት ቢሮ የማዘጋጀትና የማደስ፣ የመዋቅር፣ የሰው ኃይል ማደራጀትና የአሠራር ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት ቀድሞ የነበረውን የብድር ክፍያ ጊዜ ሰሌዳ በ15 ዓመት ለማራዘም ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ለኮርፖሬሽኑ ሥራ ውጤታማነት የኃብት አስተዳደር ሥራ ወሳኝ በመሆኑ የከተማ አስተዳደሮችና የሚመለከታቸው አካላት ለተቋሙ ውጤታማነት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም