ቀጥታ፡

በመቀሌ ከተማ ዛሬ የብስክሌት ውድድር ተካሄደ

መቀሌ ፤ ጥር 18/2016(ኢዜአ)፦ በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ ዛሬ የብስክሌት ውድድር ተካሄደ።

በነገው ዕለትም በከተማው የሩጫ ውድድር የሚካሄድ ሲሆን፤ የዛሬው የብስክሌት ውድድር "ኢትዮጵያ ትወዳደር፤ ተወዳድራ ታሸንፍ" በሚል መሪ ሀሳብ ነው የተካሄደው።

በሁለቱም ፆታዎች በተደረገው የቢስክሌት ውድድር በሴቶች ቤተልሔም ዳንኤል ከትራንስ ኢትዮጵያ አንደኛ ሆና አጠናቃለች።

ራሄል ታመነና ፃድቃን ገብረመድህን ከመስፍን ስፖርት ክለብ ሁለተኛና ሶስተኛ ወጥተዋል።

በወንዶች የተካሄደውን ውድድር ደግሞ ሀፍቶም ሀይላይ ከዓዲግራት መድሃኒት ፋብሪካ አሸንፏል።

ሰመረ ወልዳይና ክብሮም አታክልቲ ከመሶቦ ስሚንቶ ሁለተኛና ሶስተኛ ሆነው ውድድራቸውን አጠናቀዋል።


 

አሸናፊዎቹ ከውድድሩ በኋላ በሰጡት አስተያየት ውድድሩ በጣም ፈታኝ የነበረ ቢሆንም፤ በአሸናፊነት በማጠናቀቃችን ደስተኞች ነን ብለዋል።

በቀጣይም አገራቸውን በዓለም አቀፍ ውድድሮች ለመወከል ጠንክረው እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

በውድድሩ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ለወጡት ብስክሌተኞች እንደቅደም ተከተላቸው  ሽልማት ተቀብለዋል።

ሰላምን፣ፍቅርና አንድነትን የሚሰብከው የኦሎምፒክ ጨዋታ ከመጀመሩ በፊት በየአገሩ የኦሎምፒክ ችቦ ቅብብሎሽ ይደረጋል።

ችቦው ነገ በከተማዋ የሩጫ ውድድሮች ከተካሄደ በኋላ ወደ ቀጣዩ ክልል እንደሚንቀሳቀስም ተገልጿል።

ውድድሩን የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ አመራር አባላት፣ የብሄራዊ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንቶችና የመቀሌ ከተማና አካባቢው ብስክሌት ስፖርት አፍቃሪዎች ተመልክተውታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም