ቀጥታ፡

ዓለም አቀፉ የስጋ ደዌ ቀን ምክንያት በማድረግ በሐረር ከተማ የእግር ጉዞ ተካሄደ

ሐረር፤ ጥር 18 / 2016 (ኢዜአ) ፡- ዓለም አቀፉን የስጋ ደዌ  ቀን ምክንያት በማድረግ  ዛሬ  በሐረር ከተማ የተለያዩ አካላት የተሳተፉበት  የእግር ጉዞ መረሃ ግብር ተካሄደ። 

በመረሃ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ የስጋ ደዌ ተጠቂዎች ብሔራዊ ማህበር እንደገለጸው፤ "የስጋ ደዌ በሽታን አንዘንጋው" በሚል መሪ ሃሳብ  ዓለም አቀፉ የስጋ ደዌ  ቀን በአገር አቀፍ ደረጃ ነገ በሐረር ከተማ ይከበራል።

የማህበሩ ማኔጂግ ዳይሬክተር አቶ አብይ አባተ ፤  በዓሉን ምክንያት በማድረግ ዛሬ በሐረር ከተማ የእግር ጉዞ    በማድረግ ቀኑን ማሰብ መጀመሩን ተናግረዋል።

በስነ ስርዓቱም ህብረተሰቡ ስለ ስጋ ደዌ ምንነትና የተዛባ አመለካከት  ለመቀየር የሚያግዝ መልዕክት  ማስተላለፍ መቻሉን ገልጸዋል።

በዛሬው መረሃ ግብር ላይ  የኢትዮጵያ  የስጋ ደዌ ተጠቂዎች ብሔራዊ ማህበር ፕሬዝዳንትና ሌሎች አመራር አባላት፤ የሐረሪ ክልል ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የስራ ሃላፊዎችና ሰራተኞች፣የስጋ ደዌ ተጠቂዎችና ሌሎችም አካላት ተሳትፈዋል።

በነገው እለት ስጋ ደዌን ከኢትዮጵያ ለማጥፋት እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎችና  ግንዛቤ ምን እንደሚመስል በጥናት የተደገፈ የፓናል ውይይት እንደሚከናወን ተመልክቷል። 

በዚህም የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ አመራር አባላት፣ የግብረ ሰናይ ድርጅቶች ተወካዮችና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።  

የዓለም አቀፍ የስጋ ደዌ ቀን በኢትዮጵያ ለ25ኛ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ70ኛ ጊዜ ይከበራል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም