የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ ተሰሚነትና ተጽእኖ ፈጣሪነት ለማሳደግ የሚያስችሉ ጥረቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ ተሰሚነትና ተጽእኖ ፈጣሪነት ለማሳደግ የሚያስችሉ ጥረቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ
አዲስ አበባ፤ ጥር 18/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ ተሰሚነትና ተጽእኖ ፈጣሪነት ለማሳደግ የሚያስችሉ ጥረቶች ተጠናከረው የሚቀጥሉ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።
በአዲስ አበባ ላለፉት 15 ቀናት ሲካሄድ የነበረው አመታዊ የኢትዮጵያ አምባሳደሮች ጉባኤ ዛሬ ተጠናቋል::
በመድረኩም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ለአምባሳደሮቹ የስራ መመሪያና አቅጣጫ ሰጥተዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለሰ አለም (ዶ/ር) የአምባሳደሮቹን ጉባኤ መጠናቀቅ አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው መስክ የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ የሚያስችል መንገድ እየተከተለች መሆኑን በጉባኤው መመላከቱን ተናግረዋል።
በመድረኩም ኢትዮጵያ ከተለያዩ ሀገራት ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት በምታጠናክርበት ሁኔታ ላይ በስፋት ተነስቷል።
የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ ተሰሚነትና ተጽእኖ ፈጣሪነት ለማሳደግ የሚያስችሉ ጥረቶች ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።
በመሆኑም የኢትዮጵያን የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ ግንኙነት ለማጠናከር አምባሳደሮች በልዩ ትኩረት የሚሰሩ መሆኑን አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያ በቀጣናዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ መድረኮች የነቃ ተሳትፎና ትብብሯን አጠናክራ የምተቀጥል መሆኑንም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በቅርቡ የብሪክስ አባል የሆነቸው ሰፊ የዲፕሎማሲ ጥረት ተደርጎ መሆኑን አስታውሰው እድሉን በተገቢው መንገድ ትጠቀምበታለች ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራት ጋር ያላትን የዲፕሎማሲ ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልበት ጉዳይ ላይ ሰፊ ውይይት መደረጉንም ቃል አቀባዩ ገልጸዋል።
ለኢኮኖሚ ልማትና የንግድ ትብብር ግንኙነትም ልዩ ትኩረት የተሰጠው ነው ብለዋል።
አምባሳደሮቹ ከጉባኤው በተጓዳኝ በቆይታቸው በሀገሪቷ እየተገነቡ ያሉ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን መጎብኘታቸው ይታወቃል።